3. ሙሐመድ ﷺ የአላህ መልእክተኛ (የነቢያትና የመልዕክተኞች መደምደሚያ)
ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ ሰማይ ካረጉ በኋላ ወደ ስድስት መቶ ዓመታት ያህል ገደማ ረዥም ጊዜ አለፈና የሰዎችም ከቅኑ ጎዳና ማፈንገጥ ባሰ፤ ክህደት፣ ጥመትና ጣኦት አምልኮም ተሰራጨ።
ስለዚህ አላህ ሙሐመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመካ አል ሙከረማህ (በተከበረችው መካ) በሂጃዝ ምድር በምራቻና በእውነተኛ ሃይማኖት ላካቸው። አላህን ብቻውን ያለ አጋር ማምለክ፣ ነብይነታቸውንና መልእክታቸውን የሚያመለክቱ ምልክቶችንና ተአምራትን ሰጣቸው፣ በእርሱም የመልክተኛነት ማህተም፣ ሃይማኖቱንም የሃይማኖቶች ማኅተም በማድረግ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እና ቂያማም እስክትቆም ድረስ ከመቀየርና ከመለወጥ ይጠብቀዋል። ሙሐመድ ማነው?
ሕዝቦቹስ እነማን ናቸው?
እንዴትስ ተላኩ?
ከነብይነት ተአምራቶቻቸው መካከልስ ምን ምን አሉ?
የእርሳቸው የሕይወት ታሪክ ዝርዝርስ ምንድነው?
አምላክ ፈቅዶ በእነዚህ አጭር ገጾች ላይ እነዚህን ለማብራራት እንሞክራለን።
ዘራቸው እና ማህበራዊ ክብራቸው (ደረጃቸው)
እርሳቸው ሙሐመድ ቢን ዐብደሏህ ቢን ዐብዱል ሙጦሊብ ቢን ሃሺም ቢን ዓብዱል መናፍ ቢን ቁሶይ ቢን ኪላብ፤ የኢስማዒል ቢን ኢብራሂም (የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁን) ዘር፤ ከቁረይሽ ጎሣ ሲሆኑ ቁረይሽ ደግሞ ከዐረብ ነው። በ571 እ. ኤ. አ. በመካ ከተማ ተወለዱ።
አባታቸው ገና በማህፀን ውስጥ እያሉ የሞተባቸው ሲሆን በአያታቸው ዐብዱል ሙጦሊብ እንክብካቤ ሥር ወላጅ አልባ ሆነው ኖሩ። ከዚያም አያታቸውም ሲሞቱ በአጎታቸው አቡ ጧሊብ እንክብካቤ ስር ሆነው አደጉ።
ለ. ባሕርያቸው
ከፍ ብለን ለማየት እንደሞከርነው በአላህ የተመረጠ ነቢይ ከማንነት፣ ከእውነተኝነትና በጎ ስነምግባር አኳያ ከፍተኛ ስብእናን የተላበሰ ሊሆን ይገባዋል። እርሳቸውም ቢሆኑ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እውነተኛና ታማኝ፣ በመልካም ስነምግባር ያሸበረቁ፣ ልሳናቸው ጣፋጭና አንደበተ ርቱእ፣ የቅርቡም የሩቁም የሚወዳቸው፣ በማህበረሰባቸውም ዘንድ ማእረግ ያላቸው የተከበሩ፣ ታማኙ የሚል እንጅ በሌላ ቅፅል ስም የማይጠሯቸው፣ ለጉዞ ሲወጡም ሰዎች አደራ የሚጥሉባቸው ታላቅ ሰው ሆነው ነው ያደጉት።
ያላቸውን መልካም ቁመና በተመለከተ አይን አይታ የማትጠግባቸው፤ ነጭ ፊት ያላቸው፤ በሁለት ዓይናቸው መካከል ሰፊ ክፍተት ያላቸው፤ የዓይን ቅንድባቸው ረዥም፤ ፀጉራቸው ጥቁር፤ ትከሻቸው ሰፊ፤ በወንዶች መካከል ያላቸው ቁመናም ረዥምም አጭርም የማይባሉ ወደ ረዥምነት ያደሉ የተስተካከለ በአይን ታይቶ የማይጠገብ ያማረ ተክለ ሰውነት ነበራቸው። ከባልደረቦቻቸው አንዱ የገለፃቸውም እንዲህ ብሎ ነበር፦
“የአላህን መልእክተኛን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የየመን ልብስ ለብሰው አይቻቸው ነበር። ከርሳቸው የተሻለ ውብ በፍፁም አይቼ አላውቅም።”
ማንበብና መጻፍ አይችሉም ነበር፣ ማንበብና መጻፍ የማይችል ማሕበረሰብ ውስጥ ከመካከላቸው ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ጥቂት ናቸው፤ ነገር ግን ብልህ፣ ጠንካራ ትውስታ፣ ፈጣን ማስተዋል ያላቸው ነበሩ።
ሐ‐ ቁረይሾች እና ዐረቦች
ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲሁም ማህበረሰባቸው በተከበረችው የመካ ከተማ በሓረም ዙርያ አላህ ነብዩ ኢብራሂምንና ልጃቸው ኢስማዒልን (የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁን) ሊገነቡት ዘንድ ባዘዛቸው በተከበረው ካዕባ አጠገብ ነበር የሚኖሩት።
ነገር ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ከኢብራሂም ሃይማኖት (አላህን በብቸኝነት ከማምለክ) በማፈንገጥ – እነርሱም በዙሪያቸው የነበሩት ነገዶችም – በካዕባ ዙሪያ የድንጋይ፣ የዛፍና የወርቅ ጣዖታትን አበጅተው የተቀደሱ አድርገውም በመቁጠር የመጥቀምና የመጉዳት ችሎታው እንዳላቸው እስከማሰብ ደረጃም ደረሱ! ለእርሷም የአምልኮ ስርዓቶችንም ቀነጨቡላት። ከነዚህም ውስጥ በጣም ዝነኛ የሆነው የሁበል ጣኦት ሲሆን ይህ ጣኦት እጅግ ትልቁና ታላቅ ብለው የሚያስቡትም ይሀንኑ ነበር።
ከመካ ውጭ ያሉ ሌሎች ጣዖታትና ዛፎች በተመለከተ እንደ ላት፣ ዑዛና መናት ያሉት ቅዱስነትን ያላብሷቸዋል። በዙሪያቸው ካሉት አከባቢዎች ጋር የነበራቸው ሕይወት ምንም እንኳን እንደ ጀግንነት፣ እንግዳ አክባሪነትና የንግግር ሓቀኝነት መሰል መልካም ስነ ምግባሮች ቢኖሯቸውም በትዕቢት፣ ኩራትና ሌሎችን በመናቅ የተሞላ ነበር። በሌሎች ላይ ጥቃት በመሰንዘርና ዱቄት በሚያደርግ ጦርነትም የተሞላ ነበር።
መ- የነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ተልዕኮ
ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እድሜያቸው አርባ ዓመት ሲደርስና ከመካ ውጪ በሞቃታማ ምሽት በሒራእ ዋሻ ውስጥ በነበሩበት አጋጣሚ ከሰማይ የመጀመሪያው መለኮታዊ ራዕይ ከአላህ ዘንድ መጣላቸው (ወሕዩን አወረደላቸው)። መላኢካው ጂብሪል ወደ እርሳቸው መጣና ጨመቅ አድርጎ ይዞ “ኢቅራእ (አንብብ)” አላቸው፤ እርሳቸውም “እኔ አንባቢ አይደለሁም” አሉ፤ ከዚያም አሁንም ለሁለተኛ ጊዜ ጭንቅ ጥብብ እስኪላቸው ድረስ ጨመቅ አድርጎ ይዞ “ኢቅራእ (አንብብ)” አላቸው፤ እርሳቸውም “እኔ አንባቢ አይደለሁም” አሉ፤ ከዚያም ለሶስተኛ ጊዜ በጣም እስኪጨናነቁ ድረስ ጨመቅ አድርጎ ያዛቸውና “ኢቅራእ (አንብብ)” አላቸው፤ የዚህኔ እሳቸውም “ምንድን ነው የምቀራው/የማነበው?” አሉት። እሱም እንዲህ በማለት ቀጠለ፦
{አንብብ በዚያ (ሁሉን) በፈጠረው ጌታህ ስም።}
{ሰውን ከረጋ ደም በፈጠረው (ጌታህ ስም)።}
{አንብብ፤ ጌታህ በጣም ቸር ሲኾን፤}
{ያ በብዕር ያስተማረ።}
{ሰውን ያላወቀውን ሁሉ ያሳወቀ ሲኾን።}
[አልዓለቅ፡ 1_5]
ከዚያም መላኢካው ትቷቸው ሄደ። ነቢዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ፈርተውና ርደው ወደ ባልተቤታቸውና ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ለባልተቤታቸው ኸዲጃም እንዲህ አሏት፦ “በራሴ ላይ ሰግቻለሁና አልብሺኝ” ባለቤታቸውም እንዲህ አለቻቸው- “በፍጹም አላህ የሚያሳፍርህ አይነት ሰው አይደለህም! አንተኮ ዝምድናን የምትቀጥል፣ የተጨነቀን የምታግዝ፣ አስፈላጊ በሆነበት ሁሉ የምትረዳ ሰው ነህ።
ከዚያም ጂብሪል አላህ በፈጠረበት ተፈጥሯዊ አኳኃኑ ሆኖ አድማሱን ሞልቶ ወደርሳቸው መጣና እንዲህ አላቸው፦ “ሙሐመድ ሆይ! እኔ ጂብሪል ነኝ፤ አንተ (ደግሞ) የአላህ መልክተኛ ነህ።”
ከዚያም ከሰማይ ተከታታይ የሆነ ወሕይ (መለኮታዊ ራዕይ) ህዝቡን ያለምንም ተጋሪ በብቸኝነት እንዲያመልኩ እና ከሽርክና ከክህደት እንዲጠነቀቁ የሚያዝ መመርያ ይወርድ ጀመር። ነብዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ህዝባቸው ወደ እስልምና ሃይማኖት እንዲገቡ አንድ በአንድ እና በቅርበታችው ልክ እያስቀደመ ዳዕዋ (ጥሪ) ማድረጋቸውን ቀጠሉ። ዳዕዋውን የተቀበሉት የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ባልተቤታቸው ኸዲጃ ቢንት ኹወይሊድ፣ ጓደኛቸው አቡበከር አስ-ሲዲቅና የአጎታቸው ልጅ ዓሊይ ቢን አቢ ጧሊብ ናቸው። አላህ እንዲህ ብሏል፦
ከዚያም ሕዝቡ ዳዕዋቸውን እየሰማ ሲመጣ ይጋፈጧቸው፣ ያሴሩባቸውና ይተናኮሏቸው ጀመር። አንድ ቀን ጠዋት ወደ ህዝቡ ወጥተው ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ህዝቡን መሰብሰብ የፈለገ ሰው በተለምዶ የሚለውን ቃል ተጠቅመው እንዲህ አሉ “ዋ ሶባሓህ!” ብልው ተጣሩ። ህዝቡም ጥሪያቸውን እንደሰማ የሚሉትን ለመስማት ተከታትለው ተሰባሰቡ። የዛኔ እንዲህ አሏቸው፦ “እስኪ አሁን እኔ ጠላት ማልዶባችኃል ወይም መሽጎ አድሯል ብላችሁ ታምኑኛላችሁ?” ህዝቡም እንዲህ በማለት መለሰላቸው፦ “ዋሽተሀን የማታውቀውን! እንዴት አናምንህም?” የዛኔ ቀጠል አድርገው “በሉ እንግዲህ እኔ ብርቱ ከሆነ ቅጣት አስቀድሜ የማስጠነቅቃችሁ ሰው ነኝ” አሏቸው። አጎቱ አቡ ለሀብ ‐ ከአጎቶቹ አንዱ የሆነውና እርሱም ባልተቤቱም ለመልዕክተኛውና ለዲነል ኢስላም ጥልቅ ጥላቻ ያላቸው የሆኑት‐ “አፈር ብላ! ለዚህ ነው እንዴ የሰበሰብከን!” አላቸው። በዚህም የላቀው አላህ በመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ እንዲህ የሚለውን የቁርአን አንቀፆች አወረደ፦
{የአቡ ለሀብ ሁለት እጆች ከሰሩ (ጠፉ፤ እርሱ) ከሰረም።}
{ከእርሱ ገንዘቡና ያም ያፈራው ሁሉ ምንም አልጠቀመውም።}
{የመንቀልቀል ባለቤት የኾነችን እሳት በእርግጥ ይገባል።}
{ሚስቱም (ትገባለች)፤ እንጨት ተሸካሚ ስትኾን።}
{በአንገትዋ ላይ ከጭረት የኾነ ገመድ ያለባት ስትኾን።}
[አልመሰድ፡ 1_5]
ከዚያም ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ ኢስላም የሚያደርጉትን ጥሪ ቀጠሉ። ‹‹ላ ኢላሃ ኢለሏህ በሉና ነፃ ትወጣላችሁ» ይሏቸዋል። እነርሱም «አማልክቶችንም ሁሉ አንድ አምላክ አደረጋቸው፤ ይህማ እጅግ የሚደንቅ ነገር ነው።›› አሉ።
ካሉበት የጥመት ጎዳና ወጥተው ወደ ቀናው ጎዳና እንዲመጡ ጥሪ የሚያደርጉ አንቀጾችም ከአላህ ዘንድ መወረዳቸውን ቀጠሉ። በውስጣቸው ካሉት ጥሪዎችም የሚከተሉት የአላህ ቃል መጥቀስ ይቻላል፦
{በላቸው «እናንተ በዚያ ምድርን በሁለት ቀኖች ውስጥ በፈጠረው አምላክ በእርግጥ ትክዳላችሁን? ለእርሱም ባለንጣዎችን ታደርጋላችሁን? ያ (ይህንን የሠራው) የዓለማት ጌታ ነው።}
{በእርሷም ከበላይዋ የረጉ ጋራዎችን አደረገ። በእርሷም በረከትን አደረገ። በውስጧም ምግቦችዋን (ካለፉት ሁለት ቀኖች ጋር) በአራት ቀናት ውሰጥ ለጠያቂዎች ትክክል ሲኾኑ ወሰነ።}
{ከዚያም ወደ ሰማይ እርሷ ጭስ ኾና ሳለች አሰበ። ለእርሷም ለምድርም «ወዳችሁም ኾነ ወይም ጠልታችሁ ኑ» አላቸው። «ታዛዦች ኾነን መጣን» አሉ።}
{በሁለት ቀኖችም ውስጥ ሰባት ሰማያት አደረጋቸው። በሰማይቱም ሁሉ ነገሯን አዘጋጀ። ቅርቢቱንም ሰማይ በመብራቶች አጌጥን። (ከሰይጣናት) መጠበቅንም ጠበቅናት። ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው (ጌታ) ውሳኔ ነው።}
{(ከእምነት) እንቢ «ቢሉም እንደ ዓድና ሰሙድ መቅሰፍት ብጤ የኾነን መቅሰፍት አስጠነቅቃችኋለሁ» በላቸው።}
[ፉሲለት፡9_13]
ነገር ግን እነዚህ አንቀጾች እና ያ ጥሪ እውነትን ከመቀበል ይልቅ ትምክህታቸውንና ትዕቢታቸውን ብቻ ነው የጨመረላቸው። ከዛም አልፈው ወደ እስልምና ሀይማኖት የገባውን ሁሉ በተለይም የሚከላከልላቸው ወገን የሌላቸው ደካሞች የሆኑትን ሁሉ በብርቱ ማሰቃየቱን ተያያዙት። በዚህም አንዱን ሰሐባ ትልቅ ቋጥኝ በደረቱ ላይ እያስቀመጡበት፤ በዛ ከፍተኛ ሙቀት ባለው ሀገር በየገበያው እየጎተቱት ወይ በሙሐመድ ሃይማኖት ካድ አለበለዚያ ይህንን ስቃይ ወደህ ተቀበል ይሉታል። በዚህ የስቃይ ቅጣት ጥናት የሞተው እስኪሞት ድረስ ገፉበት።
የአላህ መልእክተኛን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በተመለከተ በሚወዳቸውና ከለላ በሚያደርግላቸው አጎታቸው አቡ ጧሊብ ስር ነበሩ። አጎታቸው ባለግርማና ከቁረይሽ ከበርቴዎች አንዱ ቢሆንም ወደ እስልምና ግን አልገቡም።
ቁረይሾች የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ዳዕዋ ለማጉላላት የሞከሩ ሲሆን ገንዘብ፣ ንግስናና ሌሎች ፈተናዎችንም አቀረቡላቸውና በዚህም አንድ ነገርን ብቻ እንደ ቅድመ መስፈርት አቀረቡላቸው፤ ይኸውም ከአላህ ውጭ የሚያመልኳቸውን አማልክት ከማምለክ እንዲታቀቡ የሚያዝ የሆነውን “አዲሱ” ሃይማኖት የሚያደርጉትን ጥሪ እንዲያቆሙ የሚል ነበር። በዚህ ላይ የነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አቋም ታዲያ ፍጹም ቁርጥ ያለ ፍንክች የማይል ነበር። ምክንያቱም ይህ አላህ ለሕዝቡ ያደርሱ ዘንድ የተሰጣቸው አምላካዊ መመርያ ነውና። ከዚህም መመርያ ፍንክች ቢሉ አላህ ይቀጣቸዋልና።
እኔኮ ለናንተው መልካምን (በጎን) የማስብ ሰው ነኝ፤ እናንተ ህዝብና ቤተሰቦቼ ናችሁ ነበር ያላቸው።
“ወሏሂ! (እናንተ ቤተሰቦቼን) ህዝቡን ሁሉ እንኳ ብዋሽ እናንተን አልዋሻችሁም፤ ህዝቡን ሁሉ እንኳ ላታልለው ብል እናንተን አላታልላችሁም።”
ዳዕዋውን ለማስቆም በሚያደርጉት የማጉላላት ጥረት ምንም ዓይነት ድርድር ውስጥ የማያስገባ መሆኑን እንዳረጋገጡ ቁረይሾች ለመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና ለተከታዮቻቸው ያላቸው ጥላቻም ባሰ። ቁረይሾች ነብዩ ሙሓመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ይገድሉ ዘንድ አቡ ጧሊብ አሳልፈው እንዲሰጧቸው ለዚህም በምትኩ የፈለጉትን እንደሚሰጧቸው ነገሯቸው፤ ይህን ካልቻሉ ደግሞ ቢያንስ ከመካከላቸው በሃይማኖቱ ወጣ ማለቱን እንዲያስቆሙላቸው፤ ነብዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ቢያንስ እንኳ ወደዚህ ሃይማኖት የሚያደርጉትን ዳዕዋ እንዲያስቆሙላቸው አቡ ጧሊብን ጠየቁ።
የአላህ መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ግን እንዲህ በማለት አፅንኦት ሰጥተው አቋማቸውን ሲገልፁ እንዲህ አሉ፦
“አጎቴ ሆይ! በአላህ ይሁንብኝ ይህንን የማደርገውን ጥሪ እንድተውላቸው ብለው ፀሐይን በቀኝ እጄ ጨረቃን ደግሞ በግራ እጄ ቢያስቀምጡ እንኳ እኔ ወይ አላህ እስልምናን የበላይ አድርጎ እስኪያንሰራፋው አለበለዚያም ደግሞ በዚሁ ጥሪየ ስር ሆኜ እስክሞት ድረስ ዳዕዋውን አልተወውም።”
የዚህ ጊዜ አጎታቸውም እንዲህ አሏቸው፦ “እንግዲያውስ የፈለግከውን በል! በአላህ ይሁንብኝ ባንተ በኩል የመጣን ስፋለም ልሞት እችላለሁኝ እንጅ ማንም አይደርስብህም።” አቡ ጧሊብም ሞት አፋፍ ላይ በደረሱበት ጊዜ ከእርሱ ጋር የተወሰኑ ቁረይሾችም ሳሉ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መጡ ወደ እስልምና ይገባ ዘንድ እንዲህ እያሉ ይወተውቷቸው ጀመር፦ “አጎቴ ሆይ! ላ ኢላሃ ኢለሏህ ብለህ አላህ ዘንድ መሀርታውን የምለምንልህን ቃል ተናገርልኝ” አሏቸው፤ ቁረይሾችም በፊናቸው “ከዓብዱል ሙጦሊብ (ከአባቶችህና ከአያቶችህ ሃይማኖት) ልትወጣ ነው?!” ይሏቸዋል። የአባቶቹን ሃይማኖት ትቶ ወደ እስልምና ገብቶ መሞት ከባድ አድርጎ አዩትና ሙሽሪክ እንደሆኑ ሞቱ።
ነብዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አጎታቸው በሽርክ ላይ እንዳለ መሞቱ ውስጣቸው በሃዘን ተሞላ። የላቀው አላህም እንዲህ በማለት አሳወቃቸው፦
{አንተ የወደድከውን ሰው ፈጽሞ አታቀናም። ግን አላህ የሚሻውን ሰው ያቀናል እርሱም ቅኖቹን ዐዋቂ ነው።}
[አልቀሶስ፡ 56]
ከአጎታቸው አቡ ጧሊብ ሞት በኋላ በነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ የሚደርሰው ግፉ በረታ። በካዕባ ዙርያ ሲሰግዱ (የእንስሳት) ቆሻሻ አንስተው በላያቸው ላይ ያጥሉባቸው ነበር።
ከዚያም ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሕዝቦቿን ወደ እስልምና ጥሪ ሊያደርግላቸው ወደ ጧኢፍ ከተማ (ከመካ 70 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ የሚገኝ ከተማ) ሄዱ። የጧኢፍም ሕዝቦች ከመካ ሰዎች በባሰ ሁኔታ ዳዕዋውን የተጋፈጡ ሲሆን ነብዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በሰፈር ዱርየ አስመቷቸው፤ ከጧኢፍም አባረሯቸው፤ ድንጋይ እየወረወሩም ክቡር ተረከዛቸውን እስኪያደሙ ድረስ ድበደቧቸው።
በዚህ ጊዜ ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ዱዓቸውን ወደ እርሱ በማድረግ እርዳታውንም በመማፀን ወደ አላህ ተቅጣጩ። አላህም መላኢካን ወደ እርሳቸው ላከላቸውና ‹‹ጌታህ ሕዝቦችህ ላንተ የሰጡህን ምላሽ ሰምቶአል፤ ስለዚህም ከፈለክ በሁለቱ እንጨቶች -ማለትም በሁለቱ ታላላቅ ተራሮች‐ ላጣብቃቸው›› አላቸው መላኢካው። እርሳቸውም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በፍጹም “ይልቁን እኔ የምፈልገው አላህ ከዝርያቸው እርሱን በብቸኝነት የሚያመልኩትና በአምልኮውም የማያጋሩ ባሮችን እንዲያወጣ ነው።” በማለት መለሱለት።
ከዚያም የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ መካ ተመለሱ። (ሙሽሪኮች) በእርሳቸው አማኝ ሆነው የተገኙ ህዝቦች ላይ ጥላቻና ግጭታቸውን ቀጠሉ። ከዚያም ከየሥሪብ ‐ከዚያ በኋላ መዲና ተብላ ከምትጠራው‐ ከተማ የሆኑ ጭፍራዎች ወደ መልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ እስልምና ጥሪ (ዳዕዋ) አድርገውላቸው እነርሱም ሙስሊሞች ሆኑ። ከባልደረቦቻቸውም መካከል አንዱ የሆነውን ሙስዓብ ቢን ዑመይር የተባለ ባልደረባቸውን የእስልምናን አስተምህሮት እንዲያስተምራቸው አብረው ላኩት። ከመዲና ሰዎች ብዙዎችም በእርሱ አማካኝነት እስልምናን ተቀበሉ።
በቀጣዩም ዓመት የእስልምናን ቃል ለመግባት ወደ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መጡ። ከዚያም በጭንቅ ላይ ያሉትን ባልደረቦቹን ወደ መዲና እንዲሰደዱ (ሂጅራ እንዲያደርጉ) አዘዙ። ባልደረቦቻቸውም በህብረትና በተናጠል እየሆኑ መሰደታቸውን ቀጠሉ። “ሙሃጂሮች” (ስደተኞች) የሚል ስያሜም ተሰጣቸው። የየስሪብ (መዲና) ከተማ ነዋሪዎችም በአክብሮት፣ በደስታና በመልካም ተቀበሏቸው። በቤታቸውም ውስጥ ጭምር ገንዘባቸውንና ቤታቸውንም አካፍለዋቸው ሙሃጂሮቹን ተቀበሏቸው። ከዚያም በኋላ “አንሷሮች” (ረዳቶች) የሚል ስያሜ ተሰጣቸው።
ከዚያም ቁረይሾች ይህንን የነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሂጅራ የማድረግ ውሳኔ በደረሱበት ጊዜ ነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የሚያድሩበትን ቤት በመክበብ ልክ ከቤት እንደወጡ በአንድ የብርቱ ወንድ ሰይፍ ለመግደል ወሰኑ። ከዚህም ሴራቸው አላህ መልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ጠላቶቻቸው ባላሰቡበት መልኩ ነፃ አዳናቸው። አቡበከር አስ-ሲዲቅም እርሳቸውን ተከትለው ሲሄድ ዓሊይ (አላህ የሁለቱንም መልካም ሥራቸውን ይቀበላቸው) ደግሞ ነብዩ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም ዘንድ የተቀመጡ የአደራ እቃዎች ለባለቤቶቻቸው ለመመለስ በመካ እንዲቆይ አዘዙት።
በሂጅራ ጉዟቸው ሳሉም ቁረይሾቹ ሙሐመድን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በሕይወትም ይሁን ገድሎ ለሚያመጣላቸው ሽልማት እንዳዘጋጁ አወጁ። ይሁን እንጂ አላህ መልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከባልደረባቸው ጋር በሰላም ወደ መዲና አደረሳቸው።
የመዲና ሰዎችም የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በደስታ፣ በጥሩ አቀባበልና በእርካታ ተቀበሏቸው። ሁሉም የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ለመቀበል ከየጓዳቸው ወጥተው “የአላህ መልዕክተኛ መጡ… የአላህ መልዕከተኛ መጡ… ” እያሉ ወጡ።
ነብዩም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ማረፊያቸውን ካገኙ በኋላ። በመዲናም መስጊድ መገንባትን የመጀመርያ ስራቸው አደረጉ። ከዚያም ሰዎችን የእስልምና ሕግጋትን ማስተማር፣ ቁርአንን ማስቀራትና መልካም ሥነ ምግባርን በማስተማር የእውቀት እንክብካቤ አደረጉላቸው። በዚህም ባልደረቦቻቸው ከእርሱ መመሪያውን ይማሩና ነፍሳቸውም ትጠራ እንዲሁም ስብእናቸው ከፍ ይልም ዘንድ በዙርያቸው ተሰባሰቡ። ለነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ያላቸው ፍቅር ጨመረ፤ በመልዕክተኛው ምጡቅ ስብእናም እጅግ ተማረኩ፤ በመካከላቸው ያለው የእምነት ወንድማማችነትም እጅጉን ተጠናከረ።
መዲና በርግጥም በድሃና በሃብታም፣ በነጭና በጥቁር፣ በአረብም አረብ ባልሆነውም ነዋሪዎቿ መካከል ለአላህ ባላቸው ተቅዋ እና ኢማን ካልሆነ በቀር ምንም ልዩነት የሌለባት ፍፁም የበለፀገች ተምሳሌታዊ መዲና ሆነች። ከዚህ ማህበረሰብም ታሪክ በመቼውም ጊዜ ከሚያውቀው የትውልድ ሁሉ አይነታ የሆነው ትውልድ ተፈጠረ።
ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሂጅራ የአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)ና ባልደረቦቻቸው እና የቁረይሽ ማህበረሰብንና አምሳዮቻቸው ከሆኑ የእስልምና ጠላቶች መካከል ግጭትና ፍልሚያ ተጀመረ።
በዚህ ጊዜ የመጀመርያው ታላቁ የበድር ጦርነት በመካና በመዲና መካከል በሚገኝ ሸለቆ ውስጥ ተካሄደ። አላህም በሙስሊሞች በኩል የነበሩትን ብዛታቸው 314 የሆኑ ተዋጊዎች በቁረይሽ በኩል የነበሩትን ብዛታቸው 1,000 በሆኑት ጠላቶች ላይ አበረታቸው። በዚህም ሙስሊሞቹ ከአላህ በሆነ ታላቅ እርዳታ ከቁረይሾች 70 ታላላቆቻቸው ገድለው፤ 70ዎቹንም ማርከው የተቀሩት ሸሽተው የሄዱበትን ድል ተቀዳጁ።
ከዚያም በነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና በቁረይሾች መካከል ሌሎች ፍልሚያዎችም ተካሄዱ። በመጨረሻም ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መካን (ለቀው ከወጡበት ስምንተኛው አመት በኋላ) ወደ ቁረይሾች ላይ ለመዝመት፣ በየጓሮዋ ገብተው በእነርሱ ላይ የማያዳግም ድልን ለመቀዳጀት፣ እርሱንም ለመግደል የሞከረችውን፣ ባልደረቦቹም ያሰቃየችውን፣ ከአላህ ይዞት የመጣውንም ሃይማኖት ከማሰራጨት ያገተችውን መንደር ለመውረር ወደ እስልምና ሃይማኖት የገቡ 10,000 ሰራዊቶችን አሰከትለው ወደ ተከበረችዋ መካ ዘመቱ።
ከዚያም ከዚህ እጅግ የታወቀ ድል በኋላ ሰበሰቧቸውና እንዲህ አሏቸው፦
“እናንተ የቁረይሽ ስብስቦች ሆይ! ምን ያደርገናል ብላችሁ ትገምታላችሁ?” በማለት ሲጠይቋቸው ቁረይሾቹም እንዲህ በማለት መለሱ “ቸር ወንድማችን ነህ፤ የቸር ወንድማችን ልጅም ነህ።” የዛኔ የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) “እንግዲያውስ ሂዱ እናንተ ነፃ ናችሁ!” አሏቸውና ይቅር ብለዋቸው የእስልምና ሃይማኖት የመቀበል ነፃነትን ሰጧቸው።
ይህም ሰዎች ወደ እስልምና ሃይማኖት በገፍ እንዲገቡ ምክንያት ሆነ። መላው ዓረብም በቡድን እየሆኑ ሰለሙ ወደ እስልምና ሃይማኖትም ተቀላቀሉ።
ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ እስልምና ሃይማኖት በቅርቡ የገቡ 114,000 ሰዎችን ይዘው አብረው ሐጅ አደረጉ።
በመሆኑም በዚህ ታላቁ የሓጅ ቀን የሃይማኖቱ ህግጋትንና የእስልምናን መመርያ ሊያብራሩላቸው ተነስተው ኹጥባ (ዲስኩር) ሲያደርጉ እንዲህም አሉ፦ “ምናልባት ከዚህ አመት በኋላ በመካከላችሁ ላልገኝ እችላለሁ፣ ነገር ግን አብሮኝ የነበረው አብሮኝ ላልነበረው (ሩቅ ላለው) ያድርስ” አሉና መለስ ብለው ህዝባቸውን በመመልከት እንዲህ አሉ፦ “ተልእኮየን አድርሻለሁኝን?!” አሉ፤ ባልደረቦቻቸውም “አዎ” ሲሏቸው የዚህኔ እሳቸውም መልሰው “አላህ ሆይ ምስክር ሁነኝ!” በማለት በድጋሚ “ተልእኮየን አድርሻለሁኝን?!” ብለው ጠይቁ፤ ባልደረቦቻቸውም ደግመው “አዎ” ሲሏቸው የዚህኔ እሳቸውም በድጋሚ “አላህ ሆይ ምስክር ሁነኝ!” አሉ።
ከዚያም ረሱል (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሐጅ በኋላ ወደ መዲና ተመለሱ። እናም አንድ ቀን ኹጥባ (ዲስኩር) ሲያደርጉ እንዲህ አሉ፦ “አንድ ባሪያ አምላኩ በዚህ ዓለም መዘውተር ወይስ አላህ ዘንድ ያለው ይሻለው እንደሁ ምርጫ ሰጠው፤ ያ ባርያም አላህ ዘንድ ያለውን መረጠ።” በዚህም ባልደረቦቻቸው ያ ባርያ ተብሎ የተገለፀው ራሳቸውን ለመግለፅ እንደፈለጉበትና ከዚህች አለም ህይወት ወደ አኺራ የሚሸጋገሩበት ጊዜውም እንደደረሰ የተረዱት ተረዱና ያለቀሰውም አለቀሰ። እናም በአስራ አንደኛው አመተ ሂጅራ በሶስተኛው ወር ውስጥ ባለው ሁለተኛው እለተ ሰኞ በነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ህመም ጠናባቸው። ጣእረ ሞትም ድቅን ባለባቸው ጊዜ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ ባልደረቦቻቸውን የተሰናባች እይታን እያይዋቸው ሶላታቸው ላይም እንዲጠባበቁ በአደራ አሳሰቧቸው። ክቡር ነፍሳቸውም አረፈችና ወደ ረፊቂል አዕላ (መልዕክተኞች፣ ነብያቶችና ደጋግ የአላህ ባሮች ወዳሉት) በሞት ተሸጋገሩ።
ሶሓቦች (አላህ መልካም ሥራቸውን ለሁሉ ይውደድላቸው) በነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሞት ተደናገጡ፤ ሀዘንና ትካዜያቸውም ጥግ ደረሰ፤ የመርዶው ተፅዕኖም ከእነሱ መካከል አንዱ ማለትም ዑመር ኢብኑል ኸጧብ በድንጋጤ ሰይፉን መዞ በማውጣት ማንም ሰው ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሞተዋል ሲል ብሰማው በዚህ ሰይፍ አንገቱ ነው የምቀነጥስለት እስከማለት አደረሰው።
የዚህ ጊዜ አቡበከር አስ-ሲዲቅ ተከታዩን የኋያሉ አላህን ቃል በማውሳት ገሰፀው፦
{ሙሐመድም ከበፊቱ መልክተኞች በእርግጥ ያለፉ የኾነ መልክተኛ እንጅ ሌላ አይደለም። ታዲያ ቢሞት ወይም ቢገደል ወደ ኋላችሁ ትገለበጣላችሁን ወደኋላው የሚገለበጥም ሰው አላህን ምንም አይጎዳም። አላህም አመስጋኞቹን በእርግጥ ይመነዳል።}
[አሊ-ዒምራን 144]
ዑመር ኢብኑል ኸጧብም ልክ የዚህን አንቀፅ እንደሰሙ ራሳቸውን ስተው ውደቁ፦
እኚህ ናቸው እንግዲህ የነብያቶችም የመልዕክተኞችም መደምደሚያ፣ ወደ መላው የሰው ልጅ አብሳሪና አስጠንቃቂ ተደርገው የተላኩት የአላህ መልዕክተኛ ሙሓመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)። ተልእኳቸውን አደረሱ፤ አደራቸውንም ተወጡ፤ ህዝቡንም በሚገባ መከሩ።
አላህም በተከበረውና ከሰማይ በወረደው የአላህ ቃል በሆነው ቁርኣን አጠነከራቸው፤ ያ…
{ከኋላውም ከፊቱም ውሸት አይመጣበትም። ጥበበኛ ምስጉን ከኾነው ጌታ የተወረደ ው።}
[ፉሲለት፡ 42]
ያ መላ የሰው ልጆች ከፍጥረተ ዓለሙ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ፍፃሜ ድረስ ያሉት ሰዎች ሁሉ ቢሰበሰቡና አምሳያውንም እንዲያመጡ ቢጠየቁ ከፊሉ ለሌላኛው ረዳት ሆነው እንኳ ብጤውን የማያመጡለት በሆነው ቁርአን አበረታቸው።
የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
{እናንተ ሰዎች ሆይ! የፈጠራችሁን እነዚያንም ከናንተ በፊት የነበሩትን (የፈጠረውን) ጌታችሁን ተገዙ፤ (ቅጣትን) ልትጠነቀቁ ይከጀላልና።}
{(እርሱ) ያ ለናንተ ምድርን ምንጣፍ ሰማይንም ጣራ ያደረገ ነው፤ ከሰማይም (ከደመና) ውሃን ያወረደ በርሱም ከፍሬዎች ለናንተ ሲሳይን ያወጣ ነው። እናንተም (ፈጣሪነቱን) የምታውቁ ስትኾኑ ለአላህ ባላንጣዎችን አታድርጉ።}
{በባሪያችንም ላይ ካወረድነው በመጠራጠር ውስጥ ብትኾኑ ከብጤው አንዲትን ምዕራፍ አምጡ። እውነተኞችም እንደኾናችሁ ከአላህ ሌላ መስካሪዎቻችሁን ጥሩ።}
{(ይህንን) ባትሠሩ ፈጽሞም አትሠሩትምና ያችን መቀጣጠያዋ ሰዎችና ድንጋዮች የኾነችውን እሳት ተጠበቁ፤ ለከሓዲዎች ተደግሳለች።}
{እነዚያን ያመኑትንና መልካሞችንም የሠሩትን ለነርሱ ከሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው ገነቶች ያሏቸው መኾኑን አብስራቸው። ከርሷ ከፍሬ (ዓይነት) ሲሳይን በተመገቡ ቁጥር (ፍሬዎችዋ ስለሚመሳሰሉ) «ይህ ያ ከአሁን በፊት የተገመብነው ነው» ይላሉ። እርሱንም ተመሳሳይ ኾኖ ተሰጡት። ለነሱም በውስጧ ንጹህ የተደረጉ ሚስቶች አሏቸው። እነሱም በውስጧ ዘውታሪዎች ናቸው።}
[አል-በቀራህ 21-25]
ይህ ቁርኣን ከ114 ምዕራፎች (ሱራዎች) እና ከ6,000 በላይ በሆኑ አንቀጾች የተዋቀረ ነው። አላህ ለዘመናት የሰው ልጆችን ሁሉ የቁርኣን ምዕራፎችን (ሱራዎችን) የመሰለ አንድ ምዕራፍ (ሱራ) እንኳ ማምጣት ይችሉ እንደሁ ይገዳደራቸዋል። በቁርኣን ውስጥ ካሉት ምዕራፎች አጭር የሚባለው ሱራ ሦስት አንቀጾችን ብቻ የያዘ ነው።
ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ይህ ቁርኣን ከአላህ ዘንድ መሆኑን ማወቅ አለባቸው። ይህ ታዲያ አላህ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ካጠነከረባቸው ታላላቅ ተአምራት መካከል አንዱ ነው። ያው አላህ በሌሎች ድንቅ ተአምራትም እንደደገፋቸው ሁሉ ማለት ነው። ከነዚህም መካከል፦
ረ‐ ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ካጠናከረባቸው ተአምራት መካከል፦
1- ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አላህን ተማፅነው እጃቸውን በአንዳች እቃ ላይ ያሳርፉና ውኃውም ከጣቶቻቸው ፈልቆ ይወጣል፤ ቁጥራቸው ከሺህ የሚበልጥ ሰራዊቶችም ከውሃው ይጠጡ ነበር።
2. ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አላህን ተማፅነው እጃቸውን በምግብ ማእድ ላይ ያሳርፉትና ይበረክታል፤ ቁጥራቸው ከ1500 የሚበልጥ ባልደረቦቻቸውም ከምግቡ ይበሉ ነበር።
3. ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አላህ ዝናብ እንዲያወርድላቸው በመማፀን እጃቸውን ወደ ላይ ከፍ ያደርጋሉ፤ ገና ዱዓእ ያደረጉበትን ቦታቸውንም ሳይለቁ የዝናቡ ጠብታ በሚያምር ክቡር ፊታቸው ላይ ኮለል እያለ ሲወርድ ይታይ ነበር። እንዲሁም ሌሎች በርካታ ተአምራቶችም ተሰጥቷቸዋል።
አላህ እርሳቸውንም ሊገድልና ከአላህ ዘንድ የወረደውን ይዘውት የመጡትን ብርሃን ለማጥፋት ከተነሳ ጠላት በሚያደርግላቸው ጥበቃም አጠናክሯቸዋል። ልክ የላቀው አላህ እንዲህ እንዳለን፦
{አንተ መልክተኛ ሆይ! ከጌታህ ወዳንተ የተወረደውን አድርስ። ባትሠራም መልክቱን አላደረስክም። አላህም ከሰዎች ይጠብቅሃል። አላህ ከሓዲዎችን ሕዝቦች አያቀናምና።}
[አል-ማኢዳህ: 67]
የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) – ከአላህም ድጋፍ ጋር – በተግባራቸውም ይሁን በአነጋገራቸው ሁሉ መልካም አርአያ ነበሩ። ከአላህ ዘንድ የወረደላቸውም ትእዛዝ በመፈፀም ረገድ ግንባር ቀደም ነበሩ። አምልኮና ታዛዥነትም ላይ ከሰው ሁሉ በላይ ጉጉት የነበራቸው ሲሆን ከሰዎችም ሁሉ የበለጠ ለጋስ ነበሩ። በእጃቸውም ላይ ምንም ነገር ሳያስቀሩ እንዳለ በአላህ መንገድ ላይ ለችግረኞች፣ ለድሆችና ለምስኪኖች ከመስጠት በቀር ርስት እንኳን አላስቀሩም ነበር። ለባልደረቦቻቸው እንዲህ ብለዋቸዋል፦
“እኛ የነብያት ማህበረሰቦች ቁሳዊ ውርስ አንተውም። ከንብረታችን የቀረ ነገር ቢኖር እንኳ ምፅዋት ነው።”(2)
[2] ሐዲሱን ኢማም አህመድ (2/463) ዘግበውታል፤ ሰነዱም አሕመድ ሻኪር ሙስነድን ሲያጣሩ በሰጡት ደረጃ መሰረት (19/92) ሶሒሕ ነው። (ወራሾቼ ዲናርን እንኳ አይከፋፈሉም፤ እኔ ያስቀረሁት እንኳ ቢኖር የሴት ቤተሰቦቼ መንከባከቢያና ዳዕዋዬን ለሚያግዘኝ ማጠናከሪያው ነው የሚውለው።)
በስነ ምግባርም በኩል ማንም አይደርስባቸውም ነበር። የትኛውም ሰው ሲቀርባቸው ከጥልቅ ልቡ (እጅግ በጣም) ነው የሚወዳቸው፤ ብሎም መልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከልጁ፣ ከአባቱና ከሰው ልጆችም ሁሉ አብልጦ ነው የሚወዳቸው።
የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሲያገለግላቸው የነበረው አነስ ኢብኑ ማሊክ (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው) እንዲህ ይላል፦ “ከአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መዳፍ የተሻለ ወይም የለሰለሰ ወይም ይበልጥ የሚያውድ መዳፍ ነክቼ አላውቅም። ለአስር አመታት ያክል አገልግያቸዋለሁ ስላደረግኩትም ነገር ለምን አደርግከው ስላደረግኩት ነገርም ለምን አላደረግክም ብለውኝ አያውቁም።” [3]
[3] አል-ቡኻሪ ዘግበውታል (4/230)
እኚህ ናቸው የአላህ መልዕክተኛ ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ያ የላቀው አላህ ደረጃቸውን በአለማቱ ሁሉ ከፍ ያደረገላቸው፤ ማንኛውም ሰው ድሮም ዘንድሮም የእርሳቸውን ያክል ስሙ የተወሳ የለም። ከ ሺህ አራት መቶ አመታት በፊት ጀምሮ በአለም የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አዛን አድራጊዎች በየቀኑ አምስት ጊዜ “አሽሀዱ አነ ሙሓመደን ረሱሉሏህ” በማለት ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የአላህ መልዕክተኛ መሆናቸውን ሲመሰክሩ እናም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ምዕመናንም በየለቱ በሶላታቸው ቢያንስ በአስራዎቹ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ያክል ደጋግመው “አሽሀዱ አነ ሙሓመደን ረሱሉሏህ” ይላሉ።
ሰ‐ የተከበሩት ሶሓቦች (የነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ባልደረቦች)
ከመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ህልፈት በኋላ የተከበሩት ሶሓባዎች የእስልምናን ጥሪ ኃላፊነት ተሸክመው ወደ ምድሪቱ ምሥራቅና ምእራብ በመጓዝ ዳዕዋ አደረጉ፤ እነርሱ በርግጥም የሃይማኖቱ ትክክለኛ ተጣሪዎች ነበሩ፤ ምክንያቱም ከማንኛውም ሰው በላይ እውነት ተናጋሪዎች፣ ይበልጥ ፍትሃዊ፣ ይበልጥ አደራን ጠባቂዎችና ለሰዎችም መልካምን ነገር በማካፈልም ይሁን ለሰዎች ቀናነት ይበልጥ ጉጉት የነበራቸው ሰዎች ነበሩና።
በነብያት ስነምግባር የተኮተኮቱ፤ የነብያቶችንም ኮቴ የሚከተሉ ነበሩ። ይህ ውብ ስነ ምግባራቸውም የምድሪቱ ማህበረሰቦች ዘንድ ይህንን ሀይማኖት እንዲቀበሉ የጎላ ተጽእኖ አሳድሯል። በመሆኑም ሰዎች ይህንን ሃይማኖት ከመውደድ አኳያ ያለምንም ማስገደድና አሸናፊና ተሸናፊነት ከምዕራቡ አፍሪካ እስከ ምስራቁ ኢስያ እስከ መካከለኛው አውሮፓ ክፍል ድረስ በቡድን በቡድን እየሆኑ ወደ አላህ ሃይማኖት ተከታትለው ገብተዋል።
እነርሱ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ባልደረቦች፤ ከነብያት በኋላ ከሰዎችም ሁሉ በላጭ የሆኑት ናቸው። ከእነሱ መካከል እጅግ ዝነኛ የሆኑት ከመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ህልፈት በኋላ ኢስላማዊውን ሀገራትን ሲያስተዳድሩ የነበሩት አራቱ ቅን ከሊፋዎች (ምትኮች) ናቸው። እነርሱም፦
1‐ አቡበከር አስሲዲቅ
2‐ ዑመር ኢብኑል ኸጧብ
3‐ ዑሥማን ኢብኑ ዓፋን
4‐ ዐሊይ ኢብኑ አቢ ጧሊብ
ሙስሊሞች ሰሓቦችን አስመልክቶ ታላቅ እውቅናና አድናቆት ነው የሚሰማቸው። መልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና የመልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወንድ እና ሴት ባልደረቦችን በመውደድ፣ በማላቅ፣ የሚገባቸውንም ደረጃ በመስጠት ወደ ኃያሉ አላህም ይቃረባሉ።
ሙስሊም ነኝ ብሎ ቢሞግት እንኳ በእስልምና ሃይማኖት ያስተባበለ ከሀዲ ካልሆነ በቀር ሰሓቦችን የሚጠላና የሚያነውር የለም። የላቀው አላህ እንዲህ ሲል አሞግሷቸዋልና፦
{ለሰዎች ከተገለጸች ሕዝብ ሁሉ በላጭ ሆናችሁ በጽድቅ ነገር ታዛላችሁ፤ ከመጥፎም ነገር ታዛላችሁ፤ በአላህም (አንድነት) ታምናላችሁ፡፡}
[አሊ-ዒምራን 110]
ለመልእክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ቃልኪዳን በገቡ ጊዜ አላህ ወዶ እንደተቀበለላቸው ጥራት ይገባውና እንዲህ በማለት አረጋገጠ፦
{ከምእምናኖቹ በዛፊቱ ሥር ቃል ኪዳን በሚጋቡህ ጊዜ አላህ በእርግጥ ወደደ። በልቦቻቸውም ውስጥ ያለውን ዐወቀ። በእነርሱም ላይ እርጋታን አወረደ። ቅርብ የኾነንም መክፈት መነዳቸው።}
[አል_ፈትሕ፡ 18]