መቅድም
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው።
ምስጋና ለአላህ የተገባ ነው፤ እናመስግነዋለን፤ በእርሱም እንታገዛለን፤ ምህረትንም እንጠይቀዋለን፤ ከንፍሳችን ተንኮሎች እና ከስራችን ክፋት በአላህ እንጠበቃለን፤ አላህ የመራው እርሱ የተማራ ነው፤ ያጠመመውን የሚያቀናው መሪ አታገኝለትም፤ ከአላህ በስተቀር በእውነት አምልኮት የሚገባው እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባሪያ እና መልእክተኛው መሆናቸውንም እመስክራለሁ፣ አላህ በእርሳቸው ላይ የላቀ ውዳሴ እና ሠላም ያውርድባቸው።
በመቀጠልም፦
አሁን ባለንበት ወቅት ስለ እስልምና ሃይማኖት፥ በእምነቱ ወይም በአምልኮቱ ወይም በማህበራዊ ግንኙነትም ይሁን በስርዓቱ ሆነ በሌሎቹ ዘርፍ ያለውን (ሁለንተናዊነት) አቃፊነትን እና አካታችነትን የሚዳስስ ቀላል እና አጭር ጥንቅር አስፈላጊነቱ የጎላ ነው።
ጥንቅሩን፥ አንባቢው ስለ እስልምና ሃይማኖት የተሟላ፣ አጠቃላይ እና ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖረው፤ ወደ ኢስላም የገባ ሰውም ስለ እስልምና ሃይማኖት፣ ስለ ሕግጋቶቹ፣ ስለ ስርዓቶቹ፣ ስለ ትእዛዛቶቹ እና ክልከላዎቹ ለመረዳት የመጀመሪያ ዋቢ የሚሆነውን የሚያገኝበት እንዲሆን ነው። በመሆኑም ይህ መጽሃፍ ወደ አላህ የሚጣሩ ዱዓቶች እጃቸው ላይ ይሆን እና ወደ ሁሉም ቋንቋዎች ይተረጎምና ስለ ኢስላም ለሚጠይቁ ብሎም ወደ ኢስላም ለሚገቡ ሰዎች በቀላሉ በማበርከት አላህ ለቅኑ የስኬት መንገድ ያበቃው ለስኬቱ ይበቃ ዘንድ፤ ለጠመሙት እና ለሳቱት ደግሞ ማስረጃው ይደርሳቸው ዘንድ በማሰብ ነው።
ይህንን ጥንቅር መጻፍ ከመጀመሬ አስቀድሜ፥ የዚህ መጽሃፍ ዋና ዓላማ እና ግብ ይሳካ ዘንድ፥ ጸሃፊው የሚጓዝበትን መስመር እና ደንቦች ማስቀመጥ የግድ ይላል። ከእነዚህም ደንቦች የሚከተሉትን እንጠቅሳለን፦
ይህ ሃይማኖት መቅረብ ያለበት፥ ከተከበረው ቁርኣን እና ከጠራው ነብያዊ ሐዲስ ማስረጃዎች እና ጥቅሶች ነው እንጅ፥ ከሰው የአገላለጽ ስልት አልያም በውይይት እና በማሳመን መስክ ላይ የፈላስፋዎችን ስልት በመጠቀም አይደለም፤ ይህም በተለያየ ምክንያት ነው፦
ሀ- ከፍ ያለውን የአላህን ቃል በመስማት እና መልእክቱን በሚገባ በመረዳት፥ አላህ ለስኬት ሊያበቃው የሻውን ለስኬት እንዲያበቃው እና እንዲመራው። አልያም አመጸኛ ለሆነ ጠማማ ደግሞ ማስረጃው ይደርሳቸው ዘንድ ነው፥ ከፍ ያለው ጌታ አላህ እንዲህ ብሏል፦
“ከአጋሪዎችም አንዱ ጥገኝነትን ቢጠይቅ፥ የአላህን ቃል ይሰማ ዘንድ አስጠጋው፤ ከዚያም ወደ መጠበቂያው ስፍራ አድርሰው፤ ይህ እነሱ የማያውቁ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው።”
{አተውባ፥6}
ምናልባትም በአብዛኛው ለጉድለት እና ለክፍትት በተጋለጠው በሰው የአገላለጽ ስልት አልያም የፈላስፋዎች ፍልስፍና ማስረጃ ላይረጋገጥ እና መልእክት ላይደርስ ይችላል።
ለ- አላህ ሃይማኖቱን እና ራእዩን እንደወረደ እንድናስተላልፍ ነው ያዘዘን እንጅ፥ የሰዎችን ልብ የምንማርክ መስሎን፥ የፍልስፍና አካሄድን ቀምረን እነሱን ለመምራት እንድንጓዝ አላዘዘንም፤ በመሆኑም የታዘዝንበትን ትተን ባልታዘዝነው ነገር ራሳችን ለምን ይሆን የምንወጥረው?
ሐ- ሌሎች የዳዕዋ ዘዴዎች ለምሳሌ ስለ ተቃዋሚዎች በእምነት፣ በአምልኮ፣ በስነምግባር፣ በሥነ ስርአት፣ በኢኮኖሚክስ ረገድ ያለባቸውን ስህተት በስፋት መናገር እና ለእነሱ ምላሽ መስጠት፤ ወይም የአላህን ህልውና ‐ግፈኞች ከሚሉት እጅጉን የላቀው‐ ጌታችን አላህ ህልውና ዙርያ፣ በኦሪትና በወንጌል ውስጥ ወይም በሌሎች እምነቶች ሃይማኖታዊ መፅሀፎች ላይ ስላሉ ግጭቶችና ተቃርኖዎች እንዲሁም ውድቅነት በመሳሰሉት ጉዳዮች አእምሯዊና ምልከታዊ አመክንዮዎችን በመጠቀም ማውራት እና መሰል ዘዴዎች፤
ተቃዋሚዎች ያሉበትን የተሳሳተ አቋምና የተሳሳተ እምነት ብልሹ መሆኑን ለማጋለጥ እንዲሁም ‐ባለማወቁ የማይጎዳበት ከመሆኑም ጋ‐ ለሙስሊሙም የብስለት ስንቅ ሊሆኑት ይችላሉ። ይሁን እንጅ ወደ አላህ ለሚደረግ ጥሪ የሚቆምበት መሰረታዊ ዋልታ እና መነሻ (መንደርደሪያ) ተደርጎ ሊያዝ ግን አይችልም።
መ- በእነዚህ ከላይ በተገለጹት ዘዴዎች ዳዕዋ ተደርጎላቸው ወደ እስልምና የገቡ ሰዎችም ያለ ጥርጥር እውነተኛ ሙስሊም ይሆናሉ ማለትም አይደለም። ምክንያቱም ምናልባት አንዳንዱ በተነገረው ውስን ጉዳይ ተመስጦ ወደ እስልምና ገብቶ ነገር ግን ከሃይማኖቱ መሰረቶች ምናልባትም በአንዱ የማያምን ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ በኢስላማዊ የኢኮኖሚ ሲስተም ተመስጦ በመጨረሻው ዓለም ላያምን፤ ወይንም በጂኖችና ሸይጧኖች ህልውና የማያምን ሊሆን እንደሚችለው ማለት ነው።
የዚህ ዓይነት ሰዎች ለእስልምና ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ይልቅ የሚያስከትሉት ጉዳት የበዛ ነው።
ረ- ቁርኣን ነፍሶችንና ልቦችን የመቆጣጠር ስልጣን አለው። የትኛዋም ንፁህ ህሊና ለቁርኣን ብቻ ነጻ ከሆነች፥ ጥሪውንም ትቀበለዋለች፤ በኢማንና በተቅዋም ትፋፋለች። ታዲያ በቁርኣንና በሷ መካከል ጋሬጣ መሆኑ ለምን አስፈለገ?!
ይህ ዲን ሲቀርብ አፀፋዊ ምላሾች፣ የተጨባጩ ጫናዎች እና የቀድሞ ዳራዎች መሰል ስሜቶች ጣልቃ መግባት የለባቸውም። ይልቁንም ይህ ሀይማኖት መገለፅ ያለበት ልክ በወረደበት መልኩ ሰዎችን የሚያነጋግርበትን ስልት በመከተል በፅናት ጎዳና ነው መቅረብ ያለበት።
መጽሐፉን ለመያዝም ይሁን በሰዎች መካከል ለመቀባበል ቀላል እንዲሆን የአጻጻፍ ዘይቤን ከማስፋት ይልቅ አጠር ማለቱ በተቻለ መጠን በጽሑፉ ትኩረት ተሰጥቶታል።
እንበልና ይህንን ሥራ አጠናቀን፤ መጽሐፉንም ተርጉመን፤ አሥር ሚሊዮን ቅጂዎችን አሳትመን አሥር ሚሊዮን ሰዎች እጅ ላይ ብንደርስና በዚህ መልኩም በውስጡ ባሉት የቁርኣን አንቀጾችና ሐዲሶች አንድ በመቶው ብቻ ቢያምን ከመቶ ዘጠና ዘጠኙ ደግሞ ክዶ ጀርባውን ቢሰጥ፤ አንዱ በመቶ ብቻውን አላህን ፈርቶ ኢማንና ተቅዋን ፈልጎ ወደ እኛ ቢመጣ፥ ራሱ አስበሀዋል የተከበርክ ወንድሜ! ይህ አንዱ ፐርሰንት ማለት እኮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የእስልምናን ሃይማኖት ተቀላቀሉ ማለት እኮ ነው?!
ይህ ደግሞ ታላቅ ስኬት መሆኑ የማያጠራጥር ነው። አላህም አንተን ሰበብ አድርጎህ አንድን ሰው ቢመራልህ ላንተ ከቀያይ ግመሎች የተሻለ ነው።
ኧረ እንደውም ከእነዚህ ዳዕዋ ከተደረገላቸው ሰዎች አንዳቸውም ባያምኑና ሁሉም ለዚህ ሃይማኖት ጀርባቸውን ቢሰጡ ራሱ እኛ አደራችንን ተወጥተን አላህ የሰጠንንም ኃላፊነትም አድርሰናል።
ወደ አላህ ጥሪ የሚያደርጉ ሰዎች ይበልጥ የሚያሳስባቸው ሰዎችን በዚህ ሃይማኖት ማሳመን ወይም – እንደ ቁርኣን አገላለፅ – ለመመራታቸው መጓጓት አይደለም።
{በመመራታቸው ላይ ብትጓጓ (ምንም ልታደርግ አትችልም)። አላህ የሚጠመውን ሰው አያቀናውምና።}
[አን_ነሕል፡ 37]
ይልቁን የእነሱ ዋነኛ ተልእኳቸው ልክ በልዑልና ኃያል ጌታቸው እንዲህ እንደተባሉት ነብያቸው ﷺ በተከታዩ አንቀፅ የተገለፀው ነው፦
{አንተ መልእክተኛ ሆይ! ከጌታህ ወዳንተ የተወረደውን አድርስ። ባትሠራም መልክቱን አላደረስክም። አላህም ከሰዎች ይጠብቅሃል።}
[አል-ማኢዳህ: 67]
ሁላችንም የአላህን ዲን ለመላው ሰው በማድረስ የምንተባበር፤ እንዲሁም የመልካም ነገር ቁልፎችና ወደዛም ተጣሪዎች፣ የክፋትንም በር በፊት ለፊቱ የሚዘጉ መዝጊያዎች እንዲያደርገን፥ ከፍ ያለውን እና የላቀውን አላህን እንማፀነዋለን። አላህ ይበልጡን ያውቃል፤ የአላህ ሰላትና ሰላም በነብዩ ሙሐመድ ላይ ይስፈን።