ሰ – ነቢዩ ኢብራሂም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ከዚያም አላህ ኢብራሂምን (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ህዝቦቹ ጠምመው ከዋክብትንና ጣዖታትን የሚያመልኩ በሆኑበት ጊዜ ወደ እነርሱ መልዕክተኛ ሆነው ተላኩ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
{ለኢብራሂምም ከዚያ በፊት ቅን መንገዱን በእርግጥ ሰጠነው። እኛም በእርሱ (ተገቢነት) ዐዋቂዎች ነበርን።}
{ለአባቱና ለሕዝቦቹ «ይህቺ ቅርጻ ቅርጽ ያቺ እናንተ ለእርሷ ተገዢዎች የኾናችሁት ምንድን ናት» ባለ ጊዜ (መራነው)።}
{«አባቶቻችንን ለእርሷ ተገዢዎች ኾነው አገኘን» አሉት።}
{«እናንተም አባቶቻችሁም በእርግጥ በግልጽ ስህተት ውስጥ ነበራችሁ» አላቸው።}
{«በምሩ መጣህልን ወይንስ አንተ ከሚቀልዱት ነህ» አሉት።}
{«አይደለም ጌታችሁ የሰማያትና የምድር ጌታ ያ የፈጠራቸው ነው። እኔም በዚህ ላይ ከመስካሪዎቹ ነኝ» አለ።}
{«በአላህም እምላለሁ ዟሪዎች ኾናችሁ ከሄዳችሁ በኋላ ጣዖቶቻችሁን ተንኮል እሠራባቸዋለሁ» (አለ)።}
{(ዘወር ሲሉ) ስብርብሮችም አደረጋቸው። ለእነሱ የኾነ አንድ ታላቅ (ጣዖት) ብቻ ሲቀር ወደርሱ ይመለሱ ዘንድ (እርሱን ተወው)።}
{«በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራ ማነው እርሱ በእርግጥ ከበደለኞች ነው» አሉ።}
{«ኢብራሂም የሚባል ጎበዝ (በመጥፎ) ሲያነሳቸው ሰምተናል» ተባባሉ።}
{«ይመሰክሩበት ዘንድ በሰዎቹ ዓይን (ፊት) ላይ አምጡት» አሉ።}
{«ኢብራሂም ሆይ! በአማልክቶቻችን ይህንን የሠራህ አንተ ነህን» አሉት።}
{«አይደለም ይህ ታላቃቸው ሠራው። ይናገሩም እንደ ኾነ ጠይቋቸው» አለ።}
{ወደ ነፍሶቻቸውም ተመለሱ። «እናንተ (በመጠየቃችሁ) በዳዮቹ እናንተው ናችሁም» ተባባሉ።}
{ከዚያም በራሶቻቸው ላይ ተገለበጡ። «እነዚህ የሚናገሩ አለመኾናቸውን በእርግጥ ዐውቀሃል፤» (አሉ)።}
{«ታዲያ ለእናንተ ምንም የማይጠቅማችሁንና የማይጎዳችሁን ነገር ከአላህ ሌላ ትገዛላችሁን» አላቸው።}
{«ፎህ! ለእናንተ ከአላህ ሌላ ለምትገዙትም ነገር፤ አታውቁምን» (አለ)።}
{«ሠሪዎች እንደ ኾናችሁ አቃጥሉት። አማልክቶቻችሁንም እርዱ» አሉ። (በእሳት ላይ ጣሉትም)።}
{«እሳት ሆይ! በኢብራሂም ላይ ቀዝቃዛ፤ ሰላምም ሁኚ» አልን።}
{በእርሱም ተንኮልን አሰቡ። በጣም ከሳሪዎችም አደረግናቸው።}
[አል-አንቢያእ፡ 50-70]
ከዚያም ኢብራሂም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና ልጃቸው ኢስማኢል ከፍልስጤም ወደ መካ ተሰደዱ። አላህም እርሳቸውንና ልጃቸውን ኢስማዒልን ካዕባን እንዲገነቡ አዘዛቸው፤ ሰዎችንም ወደዛው ሓጅ እንዲያደርጉ እና አላህንም እዛው እንዲያመልኩ ጋበዘ።
{ወደ ኢብራሂምና ወደ ኢስማዒልም ቤቴን ለዘዋሪዎቹና ለተቀማጮቹም ለአጎንባሾች ሰጋጆቹም አጥሩ ስንል ቃል ኪዳን ያዝን።}
[አል-በቀራህ: 125]
ሸ – ነቢዩ ሉጥ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ከዚያም በኋላ አላህ ሉጥን ወደ ወገኖቹ ላከ እነርሱም ከአላህ ውጭም የሚያመልኩ በመካከላቸውም ዝሙትን የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች ነበሩ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
{ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)። «አስቀያሚን ሥራ ትሠራላችሁን በእርሷ ከዓለማት አንድም አልቀደማችሁም።»}
{«እናንተ ከሴቶች ሌላ ወንዶችን በመከጀል በእርግጥ ትመጡባቸዋላችሁ። በእውነቱ እናንተ ወሰንን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ።»}
{የሕዝቦቹም መልስ « (ሎጥንና ተከታዮቹን) ከከተማችሁ አውጧቸው። እነሱ የሚጥራሩ ሰዎች ናቸውና» ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም።}
[አል-አዕራፍ: 80-82]
አላህ እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከከሀዲዎች ወገን ከሆነችው ሚስቱ በስተቀር አዳናቸው። ይኸውም አላህ እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመንደሩ እንዲወጡ በማዘዝ ነው። የአላህ ትእዛዝ በመጣማ ጊዜ የላይኛውን ዘቅዝቆ ወደ ታች ገለበጠው፤ ተከታታይ የሆነን የሸክላ ድንጋይም አዘነበባቸው።