የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

6- የእስልምና አስተምህሮቶች እና ስነ-ምግባር

ሀ – ትእዛዞች

እነዚህ እስልምና የሙስሊሙን ማህበረሰብ ስነምግባር ስርአት ከማስያዝ አኳያ ሊጠቀሱ ከሚችሉ አስትምህሮቶች ጥቂቶቹን አጠር ባለ መልኩ ተውጣጥተው የሚገለፁት ናቸው። እነዚህ ስነ ምግባሮች የተውጣጡትም ቁንጮ ከሆኑት ሁለቱ የእስልምና አስተምህሮት ምንጮች ማለትም ከአላህ ኪታብ (ቁርአን) እና ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሓዲሶች ነው።

አንደኛ፡ በንግግር እውነትኝነት፡-

እስልምና ሙስሊም የሆኑ ተከታዮቹን በንግግራቸው እውነተኞች እንዲሆኑ ግዴታ አድርጎባቸዋል። በምንም አይነት ሁኔታ እውነተኛ ከመሆን እንዳይወገዱም ከእነርሱው ጋር የተቆራኘ መገለጫ አድርጎታል። እንዲሁም ከውሸት ደግሞ እጅጉን ከልክሏቸዋል፤ በመጠቀ አገላለፅና በተብራራ መልኩም ከውሸት ያስጠነቅቃቸዋል። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ፍሩ፤ ከእውነተኞቹም ጋር ኹኑ።}

[አት‐ተውባህ: 119]

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

“(እናንተ ሰዎች) እውነተኝነት ላይ አደራችሁን! ምክንያቱም እውነተኝነት ወደ መልካምነት ይመራል፤ መልካምነት ደግሞ ወደ ጀነት ይመራልና። እናም አንዳችሁ እኮ እውነተኛ በመሆንና እውነትን በመምረጥ ላይ ከቀጠለ አላህ ዘንድ እውነተኛ ተብሎ ይመዘገባል። ውሸትን ተጠንቀቁ! ምክንያቱም ውሸታምነት ወደ አመፀኝነት ይመራል፤ አመፀኝነት ደግሞ ወደ ጀሀነም ይመራልና። እናም አንዳችሁ እኮ ውሸታም በመሆንና ውሸትንም በመምረጥ ከቀጠለ አላህ ዘንድ ውሸታም ተብሎ ይመዘገባል።”

[6] አል-ቡኻሪይ (6094) እና ሙስሊም (2607) ዘግበውታል።

ውሸት ከሙእሚን ባህሪያት መካከል አይደለም። ይልቁንም ከሙናፊቅ(7) ባህሪያት መካከል ነው። የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፡-

“የሙናፊቅ ምልክቱ ሶስት ነው፤ ሲናገር ይዋሻል፣ ቃል ሲገባ ቃሉን ያፈርሳል፣ ሲታመን ይክዳል።”

[7] ሙናፊቅ ሙስሊም መስሎ የሚታይ ሰው ቢሆንም ነገርግን በእውነታው እና በልባዊ እምነቱ በእስልምና ሀይማኖት የሚያምን አማኝ አይደለም።

[8] ሐዲሱ አል-ቡኻሪይ (1/15) ላይ: ኪታቡል ኢማን: ዓላማቱል ሙናፊቅ በሚል ባብ ስር ዘግበውታል።

ለዚህም ነው ከመካከላቸው አንዱ “በአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ዘመን መዋሸት የሚባልን ነገር አናውቀውም ነበር” እስኪል ድረስ የተከበሩ ሶሓቦች በእውነተኛነት ላይ ጥብቅ አቋም የነበራቸው።

ሁለተኛ፡ አደራን መወጣት፣ ቃል ኪዳኖችን መሙላት እና በሰዎች መካከል ፍትህን ማስፈን

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{አላህ አደራዎችን ወደ ባለቤቶቻቸው እንድታደርሱ ያዛችኋል፡፡ በሰዎችም መካከል በፈረዳችሁ ጊዜ በትክክል እንድትፈርዱ (ያዛችኋል)፡፡}

[ኒሳእ: 58]

አላህ -ጥራት ይገባውና- እንዲህም ይላል፦

{በኪዳናችሁም ሙሉ፡፡ ኪዳን የሚጠየቁበት ነውና።}

{በሰፈራችሁም ጊዜ ስፍርን ሙሉ። በትክክለኛው ሚዛንም መዝኑ። ይህ መልካም ነገር ነው። መጨረሻውም ያማረ ነው።}

[አልኢስራእ፡ 34_35]

ምእመናኑንም እንዲህ በማለት አወድሷቸዋል፦

{እነዚያ በአላህ ቃል ኪዳን የሚሞሉ የጠበቀውንም ኪዳን የማያፈርሱ ናቸው።}

[አር-ራዕድ: 20]

ሦስተኛ፡ ትሕትና እና አለመኩራራት፡-

ነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እጅግ በጣም ትሁት ከሆኑ ሰዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን ከሶሃቦቻቸው መካከል እንደ አንዱ ሆነው የሚቀመጡ፤ መጡ ተብለው ሰዎች እንዲቆሙላቸው እንኳ የሚጠሉ ነበሩ። ሙስሊሞችንም ትሁት እንዲሆኑ እንዲህ በማለት አዘዋቸዋል፡- (አላህ አንዱ በሌላው ላይ እንዳይኮራበትና አንዱ በሌላው ላይ ድንበርን እንዳያልፍበት እርስ በእርሳችሁ እንድተናነሱ ወሕይ (ራእይ) አውርዶልኛል[9]።)

[9] ሐዲሱን በሙስሊም (17/200) ኪታቡል ጀናህ: የጀነት ሰዎች የሚታወቁባቸው ባህሪያት በሚል ባብ ስር ዘግበውታል።

አራተኛ፡ ልግስና፣ ቸርነት እና በበጎ አድራጎት ጉዳዮች ላይ ገንዘብን ማውጣት፡-

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{ከገንዘብም የምትለግሱት (ምንዳው) ለነፍሶቻችሁ ነው። የአላህንም ፊት (ውዴታውን) ለመፈለግ እንጂ አትለግሱም። ከገንዘብም የምትለግሱት ሁሉ (ምንዳው) ወደናንተ ይሞላል። እናንተም አትበደሉም።}

[አልበቀራህ፡ 272]

አላህ ምእመናንን እንዲህ ሲል አሞግሷቸዋል፦

{ምግብንም ከመውደዳቸው ጋር ለድኻ፣ ለየቲምም፣ ለምርኮኛም ለእስረኛም ያበላሉ።}

[አልኢንሳን፡ 8]

ልግስና እና ቸርነት የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና የእርሳቸውን ፈለግ የተከተሉ ምእመናን ባህሪ ናቸው። በዚህ ረገድ ምንም ገንዘብ ቢኖራቸው ለበጎ አድራጎት ከማዋል አይሰስቱም ነበር። ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ባልደረቦች አንዱ ጃቢር (አላህ መልካም ሥራቸውን ይውደድላቸው) ስለሳቸው እንዲህ ብለዋል፡-

“የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ምንም ነገር ተጠይቀው እምቢ ብለው አያውቁም።”

እንግዳ ማክበርን በማስመልከትም እንዲህ ሲሉ አነሳስተዋል፦

{“በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ ጎረቤቱን አያስቸግር፤ በአላህና በመጨረሻው ቀን ያመነ እንግዳውን ያክብር፤ በአላህና በመጨረሻው ቀን መልካምን ይናገር አሊያም ዝም ይበል።”

[10] አል ቡኻሪ (6138) እና ሙስሊም (47) ዘግበውታል።

አምስተኛ: ትዕግስት እና ችግርን መቋቋም:

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገስ፡፡ ይህ በምር ከሚያዙ ነገሮች ነው።}

[ሉቅማን፡ 17]

አላህ -ጥራት ይገባውና- እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! በመታገስና በሶላት ተረዱ። አላህ (በእርዳታው) ከታጋሾች ጋር ነውና።}

[አልበቀራህ፡ 153]

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያንም የታገሱትን ይሠሩት በነበሩት በመልካሙ ምንዳቸውን እንመነዳቸዋለን።}

[ነሕል፡ 96]

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እጅጉን ታጋሽ እና ችግርን የሚቋቋሙ እንዲሁም የማይበቀሉ ነበሩ። ህዝባቸውን ወደ እስልምና ሲጣሩ ህዝባቸው ግን እስኪደሙ ድረስ ደብድበዋቸዋል። እርሳቸው ግን የፊታቸውን ደም እያበሱ እንዲህ ነበር ያሉት፡-

(አላህ ሆይ! ህዝቦቼ ባለማወቃቸው ነውና ይቅር በላቸው።) [11]

[11] ሐዲሱን አል-ቡኻሪይ ኪታቡል ሙርተዲን በሚለው (5ኛው) ስር (9/20) ዘግበውታል።

ስድስተኛ፡ ሓያእ (አይናፋርነት)፡‐

ሙስሊሙ ጥብቅ እና አይናፋር ነው። አይናፋርነትም ከእምነት ቅርንጫፎች አንዱ ሲሆን ሙስሊምን ለመልካም ባህሪያት ሁሉ ያነሳሳዋል፤ ለሓያኡ ባለቤትም በቃልም ሆነ በተግባሩ ከብልግና እና ጸያፍ ነገሮች ያቅበዋል። በርግጥ የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፡-

“ሓያእ ይዞ የሚመጣው ኸይርን (መልካምን) ብቻ ነው።” [12]

[12] ሐዲሱን አል-ቡኻሪይ ኪታቡል አደብ: አልሓያእ በሚለው ባብ ስር (8/35) ዘግበውታል።

ሰባተኛ፡ ለወላጆች በጎ መዋል፡-

ወላጅን ማክበር፤ ለነርሱ በጎን መዋል፤ በመልካም ሁኔታ መኗኗር እና የመዋረድ ክንፍን ለእነርሱ ዝቅ ማድረግ በእስልምና ሀይማኖት ውስጥ ካሉ መሰረታዊ ግዴታዎች መካከል ናቸው። ወላጆች ወይንም አንዳቸው እርጅና ሲጫጫናቸው እና የልጃቸውንም ይበልጥ ፈላጊ ሲሆኑ ደግሞ ይህ ግዴታ ይበልጥ አፅንኦት የተሰጠው ይሆናል። በእርግጥም የላቀው አላህ በታላቁ ኪታቡ (በቁርአን) ለእነርሱ በጎ መዋልን አዟል እንዲሁም የነርሱን ሓቅ ታላቅነትንም አፅንኦት ሰጥቶታል። ጥራት ይገባውና እንዲህ ብሏል፦

{ጌታህም (እንዲህ ሲል) አዘዘ፡- እርሱን እንጂ ሌላን አትገዙ፡፡ በወላጆቻችሁም መልካምን ሥሩ። በአንተ ዘንድ ኾነው አንዳቸው ወይም ሁለታቸው እርጅናን ቢደርሱ ፎህ አትበላቸው። አትገላምጣቸውም። ለእነርሱም መልካምን ቃል ተናገራቸው።}

{ለሁለቱም ከእዝነትህ የመዋረድን ክንፍ ዝቅ አድርግላቸው። «ጌታዬ ሆይ! በሕፃንነቴ (በርኅራኄ) እንዳሳደጉኝ እዘንልላቸውም» በል።}

[አልኢስራእ፡ 23_24]

አላህ -ጥራት ይገባውና- እንዲህ ብሏል፦

{ሰውንም በወላጆቹ (በጎ እንዲያደርግ) በጥብቅ አዘዝነው፡፡ እናቱ ከድካም በላይ በሆነ ድካም አረገዘችው፡፡ ጡት መጣያውም በሁለት ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ለእኔም ለወላጆችህም አመስግን በማለት (አዘዝነው)፡፡ መመለሻው ወደኔ ነው።}

[ሉቅማን:14]

አንድ ሰው ነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፡- “መልካም መስተጋብሬ ይበልጥ የሚገባው ማን ነው?” አላቸው።

(“እናትህ” አሉት፤ “ከዚያስ ማን?” አለ፤ “እናትህ” አሉት፤ “ከዚያስ ማን?” አለ፤ “እናትህ” አሉት፤ “ከዚያስ ማን?” ሲላቸው ”አባትህ” በማለት መለሱለት። [13]

[13] ሐዲሱን አል-ቡኻሪ ኪታቡል አደብ መን አሐቁናሲ ቢሑስኒ ሱሕባህ በሚል ባብ ስር(8/2) ተዘግቧል።

ስለዚህም እስልምና እያንዳንዱን ሙስሊም አላህን በማመፅ ጉዳይ ላይ ካልሆነ በቀር ወላጆቹን ያዘዙትን ነገር ሁሉ እንዲታዘዝ ግዴታ አድርጓል። አላህን በማመፅ ጉዳይ ላይ ሲሆን ግን ፈጣሪን በማመፅ ላይ ፍጡርን መታዘዝ የሚባል ነገር የለም። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል:

{ለአንተ በእርሱ ዕውቀት የሌለህን ነገር በእኔ እንድታጋራ ቢታገሉህም አትታዘዛቸው፡፡ በቅርቢቱም ዓለም፤ በመልካም ሥራ ተወዳጃቸው፡፡}

[ሉቅማን: 15]

እነሱን ማክበር፣ የመተናነስ ክንፉን ለነርሱ ዝቅ ማድረግ፣ በቃልም በተግባርም አክብሮት መስጠት እንዲሁም መመገብ፣ ማልበስ፣ ሲታመሙ ማሳከም፣ ችግር እንዳያገኛቸው በተቻለ አቅም መጣር በመሳሰሉት ፅድቅ ነገሮችም ሁሉ ለነርሱ በጎ መዋልም ግዴታ ተደርጓል። ለእነርሱ ዱዓእ ማድረግ፣ መሀርታን መለመን፣ ቃል የገባንላቸውን መፈፀምና ጓደኞቻቸውን እንኳ ማክበርም ለነርሱ በጎ መዋል ውስጥ የሚካተቱ ግዴታዎች ናቸው።

ስምንተኛ፡ ከሌሎች ጋር መልካም ስነምግባር

ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

(ከሙእሚኖች መካከል ይበልጥ ኢማናቸው የተሟሉት በመልካም ሥነ-ምግባር በልጠው የተገኙት ናቸው።) [14]

(14) ሐዲሱን አቡ ዳውድ በኪታቡ ሱና፣ አድደሊሉ ዓላ ዚያደቲ ወኑቅሷኒህ በሚል ባብ ስር (5/6) እንዲሁም ቲርሚዚይ ኪታቡ ረዷዓህ፣ ማጃአ ፊ ሓቂል መርአቲ ዓላ ዘውጂሃ በሚል ባብ ስር (3/457) ዘግበውታል፤ ቲርሚዚይ ሓዲሱን ሓሰኑን ሶሒሕ ብለውታል፤ አልባኒይ የሰጡትን ደረጃ ለማየት ደግሞ ሶሒሕ አቢ ዳውድ (3/886) መመልከት ይቻላል።

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

“ከናንተ መካከል እኔ ዘንድ በጣም የተወደዳችሁትና በቂያማ ቀንም ለእኔ ይበልጥ ቅርብ የሆነ ደረጃ ያላችሁ ከእናንተ በሥነ ምግባር በላጭ የሆናችሁት ናችሁ።” [15]

[15] ሐዲሱን ቡኻሪይ ኪታቡል መናቂብ: ሲፈቱን ነቢይ ሶለሏሁ ዓለይሂ ወሰለም በሚል ባብ ስር (4/230) በሌላ የቃል አጠቃቀም ዘግበውታል።

አላህ ነብዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ሲል ገልጿቸዋል፦

{አንተም በታላቅ ጠባይ ላይ ነህ።}

[አል-ቀለም 4]

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

(እኔ የተላክሁት መልካም ስነምግባርን ላሟላ ነው።) [16]

ስለዚህም እያንዳንዱ ሙስሊም ከላይ እንደገለፅነው ከወላጆቹ ጋር ባለው መስተጋብሩ መልካም ባህሪን መላበስና መልካም ሊሆንላቸውም ይገባል። ልክ ወላጆችም ከልጆቻቸው ጋር በመልካም ስነምግባር በማነፅ፣ የእስልምና አስተምህሮትንም በማስተማር እንዲሁም በዱንያም ይሁን በአኼራቸው ከሚጎዳቸው ነገርም ሁሉ እያስጠነቀቀ እንዲሁም ከገንዘቡም ሳይሰስትባቸው ራሳቸውን እስኪችሉና የራሳቸው የገቢ ምንጭም እስኪያመቻቹ ድረስ እየለገሰ ማሳደግ እንዳለበት ሁሉ ማለት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ ከሚስቱ፣ ከወንድሞቹ፣ ከእህቶቹ፣ ከዘመዶቹ፣ ከጎረቤቶቹና ከሁሉም ሰዎች ጋርም መልካም ባህሪ ያለው ለራሱ የሚወደውን ለወንድሞቹ የሚወድ ሊሆን ይገባል። ዝምድናውንም ጉርብትናውንም እየቀጠለ፣ ታላቆቹንም እያከበረ ለታናሾቹም እየራራ፣ ችግርተኞችንም እያፅናና ተከታዩን የአላህ ቃል ከመፈፀም አኳያ ጥሩ ስነምግባርን ይላበስ፡-

{በወላጆችና በቅርብ ዝምድና ባለቤትም፣ በየቲሞችም፣ በምስኪኖችም፣ በቅርብ ጎረቤትም፣ በሩቅ ጎረቤትም፣ በጎን ባልደረባም፣ በመንገደኛም መልካምን (ሥሩ)}

[አን-ኒሳእ: 36]

እንዲሁም ተከታዩን የነቢዩን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ቃልም ከመፈፀም አኳያ፡

(በአላህና በመጨረሻው ቀን የሚያምን ጎረቤቱን አያስቸግር።) [17]

[16] ሐዲሱን ኢማሙ አህመድ በአል-ሙስናድ (17/80) የዘገበው ሲሆን አህመድ ሻኪርም ኢስናዱ ሶሒሕ ነው ብለዋል፤ ቡኻሪይም በአል-አዳብ ፣ አል-በይሃቂይ ደግሞ በሹዐብ አል- ኢማን፣ እንዲሁም አል-ሀኪም በአል-ሙስተድረክ ላይ ዘግበውታል።

[17] ሐዲሱን ቡኻሪይ በኪታቡል አዳብ፡ መን ካነ ዩእሚኑ ቢላሂ ወል የውሚል አኺር ፈላ ዩእዚ ጃረሁ በሚል ባብ ስር (8/13) ዘግበውታል።

ዘጠነኛ፡ ተበዳይን ለመደገፍ፣ ሓቅን ወደ ባለቤቱ ከመመለስ እና ፍትህ ከማስፈን አኳያ በአላህ መንገድ ጂሃድ ማድረግ

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያንም የሚጋደሉዋችሁን (ከሓዲዎች) በአላህ መንገድ ተጋደሉ። ወሰንንም አትለፉ፤ አላህ ወሰን አላፊዎን አይወድምና።}

[አልበቀራህ፡ 190]

ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{በአላህ መንገድና ከወንዶች ከሴቶችና ከልጆችም የኾኑትን ደካሞች እነዚያን፡- «ጌታችን ሆይ! ከዚች ባለቤቶችዋ በዳይ ከኾኑት ከተማ አውጣን ከአንተም ዘንድ ለእኛ አሳዳሪን አድርግልን ከአንተ ዘንድም ለእኛ ረዳትን አድርግልን» የሚሉትን (ለማዳን) የማትጋደሉት ለእናንተ ምን አላችሁ}

አንኒሳእ፡ 75]

የኢስላማዊ ጂሃድ አላማ እውነትን ማግኘት፣ ፍትህን በሰዎች መካከል ማስፈን፣ ሰዎችን የሚጨቁኑ እና የሚያሰቃዩ ሰዎችን መዋጋት እና አላህን ከማምለክ እና የእስልምናን ሀይማኖት እንዳይቀበሉ ማድረግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችን ማስገደድ የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ያደርጋል። በግዳጅ ወደ እስልምና ሀይማኖት ስለ መግባት ኃያሉ አምላክ እንዲህ ብሏል፡-

{በሃይማኖት ማስገደድ የለም፡፡}

[አልበቀራህ፡ 256]

በጦርነት ጊዜ አንድ ሙስሊም፦ ሴትን፣ ትንሽ ልጅን ወይም ሽማግሌን መግደል አይፈቀድለትም፤ ይልቁንም ፍትሃዊ ያልሆኑ ተዋጊዎችን ይዋጋል።

በአላህም መንገድ የተገደለ ሁሉ ሰማዕት ነውና በአላህ ዘንድ ማዕረግ፣ ምንዳና ምንዳ አለው። ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{እነዚያን በአላህ መንገድ የተገደሉትን ሙታን አድርገህ አትገምታቸው። በእርግጥ እነርሱ እጌታቸው ዘንድ ሕያዋን ናቸው፤ ይመገባሉ።}

{አላህ ከችሮታው በሰጣቸው ነገር ተደሳቾች ሲኾኑ (ይመገባሉ)። በነዚያም ከኋላቸው ገና በእነርሱ ባልተከተሉት በእነርሱ ላይ ፍርሃት ባለመኖሩና እነርሱም የማያዝኑ በመኾናቸው ይደሰታሉ።}

[አሊ-ዒምራን 169 – 170]

አስረኛ፡ ዱዓእ፣ ዚክር እና ቁርኣን መቅራት፡-

የአንድ አማኝ እምነት በጨመረ ቁጥር ከላቀው አላህ ጋር ያለው ቁርኝት፣ እርሱን መማፀኑ እና በዚህ ዓለም ጉዳዩን እንዲያሟላለት፣ በአኼራው ደግሞ ኃጢአትና ክፋቶቹንም ይቅር እንዲልለት ብሎም ደረጃው ከፍ እንዲልለት በእርሱ ፊት ያለው መተናነስ ይጨምራል። አላህ ጠያቂ ሁሉ ቢጠይቀው የሚወድ ቸር አምላክ ነው። ጥራት ይገባውና እንዲህ ብሏል፦

{ባሮቼም ከእኔ በጠየቁህ ጊዜ (እንዲህ በላቸው)፡- እኔ ቅርብ ነኝ፡፡ የለማኝን ጸሎት በለመነኝ ጊዜ እቀበለዋለሁ፡፡}

(አልበቀራህ፡186)

አላህ ለባሪያው የሚበጀውን ዱዓእ ይቀበለዋል፤ ብሎም ስለለመነውም መልካም ምንዳንም ይቸረዋል።

እንደዚሁ ከምእመናን ባህሪያት መካከል ሌትም ቀንም በድብቅም ይሁን በግልጽ ደጋግሞ የላቀው አላህን የሚያወድስ መሆኑ ነው። ስለዚህም በተለያየ የውዳሴና ማላቅ አይነት አላህን ያወድሰዋል ያልቀዋልም፤ ለምሳሌ በሚከተለው አኳኃን፡- ሱብሓነሏህ (ጥራት ለአላህ ይገባው)፣ አልሓምዱሊላህ (ምስጋና ለአላህ ይገባው)፣ ላኢላሃ ኢለሏህ (ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ የለም)፣ አሏሁ አክበር (አላህ ታላቅ ነው) እና ሌሎችም የላቀው አላህ እንዲወሳባቸው የተደነገጉ የውዳሴ አይነቶች ሁሉ አላህን ማወደስና ማላቅ የሙእሚን ባህሪይ ነው። ለዚህም የላቀው አላህ ከፍ ያለ አጅርንና ታላቅ ምንዳን አዘጋጅቷል። የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

(“`ሙፈሪዶች` ቀድመው ሄዱ” አሉ “ያረሱለሏህ! “ሙፈሪዶች” እነማን ናቸው? በማለት ሰሓቦች ሲጠይቋቸው እሳቸውም “አላህን አብዝተው የሚያወሱ ወንዶችና አብዝተው የሚያወሱ ሴቶች ናቸው” በማለት መለሱላቸው።) [18]

አላህ -ጥራት ይገባውና- እንዲህም ብሏል፦

{እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አላህን ብዙ ማውሳትን አውሱት።}

{በቀኑ መጀመሪያና መጨረሻም አጥሩት። አስታውሱኝም፤} [አልአሕዛብ፡ 41_42] {አስታውሳችኋለሁና ለኔም አመስግኑ፤ አትካዱኝም።}

[አልበቀራህ፡ 152]

የአላህን ኪታብ – የተከበረው ቁርኣንን – መቅራት አላህን ከማውሳት ነው። አንድ ሰው ቁርኣን መቅራቱን እና ማስተንተኑን ባበዛ ቁጥር በአላህ ዘንድ ያለው ደረጃም ይበልጥ ከፍ እያለ ይሄዳል።

[18] ሐዲሱን ሙስሊም ኪታቡ ዚክሪ ወዱዓእ: አልሓሡ ዓለዚክር በሚለው ባብ ስር (17/4) ዘግበውታል።

ቁርኣንን ሲቀራ ለነበረ ሰው በእለተ ትንሳኤ እንዲህ ይባላል፦

(ቁርአንን ቅራ እና ወደ ላይ ውጣ፤ ልክ በዱንያ ሳለህ ስትቀራ እንደነበርከው አድርገህ ቅራ፤ ዛሬ ደረጃህ መቅራትህን ባቆምክበት አንቀጽ ነውና የሚገደበው።) [19]

[19] በአቡ ዳውድ (1464) የዘገበው ሲሆን ቃላቱ የእሱ ነው፤ ቲርሚዚይም (2914)፣ ነሳኢይም በ (አስ-ሱነን አል-ኩብራ) (8056) እና አህመድ (6799) ዘግበውታል።

አስራ አንደኛው፡ የሸሪዓን እውቀት መማር፣ ሰዎችን ማስተማር እና ወደዛውም ስለ መጣራት፡-

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፦

(እውቀትን ፍለጋ መንገድን የጀመረ አላህ የጀነት መንገድን ያገራለታል። መላኢኮችም ዕውቀት ፈላጊ ለሆነ ሰው በሚያደርገው ነገር ተደስተው ክንፎቻቸውን ዝቅ ያደርጉለታል።) (20)

[20] ሐዲሱን ቲርሚዚ የእውቀት ምዕራፎች: ፈድሉል ፊቅሂ ፊ ዲን በሚለው ባብ ስር (4/153)፤ አቡ ዳውድ ኪታቡል ዒልም: አልሓሡ ዓላ ጦለቢል በሚለው ባብ ስር (4/5857)፤ ኢብኑ ማጃህ ገና በመግቢያው (1/81) ዘግበውታል። አልባኒይ ደግሞ በሰሒሑል ጃሚዕ ሶሒሕ ነው ብለዋል (5/302)

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህም ብለዋል፦

(ከናንተ በላጩ ቁርኣንን ተምሮ እና ያስተማረ ነው።)[21]

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህም ብለዋል፦

(በእርግጥ መላእክት ለሰዎች መልካምን እውቀት ለሚያስተምሩ ሰዎች ሶለዋትን ያወርዳሉ።) [22]

የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህም ብለዋል፦

(ወደ ቀናነት ዳዕዋ ያደረገ ሰው በዳዕዋው ምክንያት የሰሩት ሰዎች አምሳያ አጅር አለው፤ የነርሱ ምንዳም ከቶ ምንም ሳይቀነስባቸው።) [23]

[21] ሐዲሱን ቡኻሪይ ኪታቡል ፈዷኢል: ኸይሩኩም መን ተዓለመል ቁርአነ ወዓለመህ በሚል ባብ ስር (6/236) ዘግበውታል

[22] ሐዲሱን ቲርሚዚይ ኪታቡል ዒልም: ማ ጃአ ፊ ፈድሊል ፊቅሂ ዓለል ዒባዳህ በሚለው ባብ ስር (5/50) ረዘም ባለ አውድ ዘግበውታል።

[23] ሙስሊም ኪታቡል ዒልም: መን ሰነ ሱነተን ሓሰነተን አው ሰይአተን በሚለው ባብ ስር (16/227) ዘግበውታል።

አላህ -ጥራት ይገባውና- እንዲህም ይላል፦

{ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሠራ፣ «እኔ ከሙስሊሞች ነኝ» ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?}

[ፉሲለት፡ 33]

አስራ ሁለተኛው፡ በአላህና በመልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ፍርድ ስለመርካት፡-

አላህ የደነገገውን ትእዛዝ አለመቃወም፤ አላህ ከፈራጆች ሁሉ ጥበበኛ ከአዛኞችም ሁሉ በጣም አዛኝ፤ በምድርም በሰማይም ከርሱ የተደበቀ አንዳችም ነገር የሌለ፤ ፍርዱ በባሪያዎቹ ስሜታዊነትም ይሁን በግፈኞች ስግብግብነት የማይነካ ነውና። ከእዝነቱ መገለጫዎች መካከል ለባሮቹ በቅርቢቱም ሆነ በመጨረሻይቱ ዓለም የሚጠቅማቸውን እና ከአቅማቸው በላይ የማይችሉት የሆነን መመርያ አለማውጣቱ ነው። ለእርሱ ባርያ መሆን ከሚያስፈርዳቸው እውነታዎች መካከል ልባዊ ከሆነ እርካታ ጋር ወደርሱ ህግ መፋረድና በፍርዱም መደሰት ግድ ነው።

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{በጌታህም እምላለሁ በመካከላቸው በተከራከሩበት ፍርድ እስከሚያስፈርዱህ ከዚያም ከፈረድከው ነገር በነፍሶቻቸው ውስጥ ጭንቀትን እስከማያገኙና ፍጹም መታዘዝንም እስከሚታዘዙ ድረስ አያምኑም፤ (ምእመን አይኾኑም)።}

[አን_ኒሳእ፡ 65]

[አልማኢዳህ፡ 50]

ለ – ሐራምና ክልክል ስለሆኑ ነገሮች

አንደኛ፡- ሽርክ፡ (የትኛውንም አይነት የአምልኮ ዓይነት ከአላህ ውጭ ላለ አካል አሳልፎ መስጠት)

About The Author