5- የእምነት ማዕዛናት
የእስልምና ማዕዘናት ሙስሊሙ የሚላበሳቸው ውጫዊ መገለጫዎች መሆናቸውን እና እነርሱን መተግበሩም የእስልምናን ሃይማኖት መቀበሉን የሚያመለክቱ እውነታዎች መሆናቸው ካወቅን ዘንዳ ሙስሊሙ የእስልምናው ትክክለኝነት እውን ሊሆን ዘንድ ልቡ ውስጥ ሊያምንባቸው የሚገቡ “አርካኑል ኢማን” የሚባሉ ማዕዘናትም አሉ። እነኝህ ማዕዘናት ይዘታቸው በሙስሊሙ ልቦና ውስጥ በጨመሩና በተሟሉ ቁጥር በኢማን ያለውም ደረጃም እየላቀ በአላህ ሙእሚን ባርያዎች ውስጥ ለመጠቃለል ይበልጥ የተገባ እየሆነ ይሄዳል። ይህች (የሙእሚኖች) ደረጃ ታዲያ ከሙስሊሞች ደረጃ ከፍ ያለች ነች፤ ምክንያቱም የሙእሚንነት ደረጃ የደረሰ ሁሉ ሙስሊም ነውና፤ ሙስሊም የሆነ ሁሉ ግን የሙእሚንነት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት አይደለም።
በእርግጥ በመሰረታዊነት የኢማን መሰረቱ አለው፤ ነገር ግን በተሟላ መልኩ ላይሆን ይችላል።
የእምነት ማዕዘናት ስድስት ናቸው:
(በአላህ፣ በመላዕክቱ፣ በመጻሕፍቱ፣ በመልክተኞቹ፣ በመጨረሻው ቀን ማመን እና በቀደር መልካምም ሆነ መጥፎ በሆነ (የአላህ ቅድመ ውሳኔ) ማመን ነው)።
የመጀመሪያው ማዕዘን፡- በአላህም ልታምን እና ልቦናህም አላህን በመውደድ፣ እርሱንም በማላቅ፣ እርሱ ዘንድም ራስህን የተዋረድክ መሆንህንና ተሸናፊነትህንም ልታጎላ፣ ለእርሱም ትእዛዛት ያለምንም ተጋሪ ታዛዥ በመሆን ልቦናህን ልትሞላ እንዲሁም እርሱን በመፍራትና እርሱም ዘንድ ያለውን በመከጀል ልቦናህ የተሞላ ሊሆን እንደሚገባው ሁሉ ማለት ነው። በዚህ ሁኔታም አላህን ከሚፈሩትና የእርሱን ቀና ጎዳና ከሚጓዙት የአላህ ባርያዎች ይሆናል።
ሁለተኛው ማዕዘን፡- በመላእክት ማመን ሲሆን እነርሱም ከብርሃን የተፈጠሩ የአላህ ባሮች መሆናቸውን፤ ከአላህ በቀር ቁጥራቸው ያማያውቅ፣ በሰማይና በምድር ያሉ ተቆጥረው የማይዘለቁ፤ አላህን በማምለክ፣ በማወደስና ከማይገባው በማጥራት (ተስቢሕ በማድረግ) ማንነት ተደርገው እንደተፈጠሩና ሌትም ቀንም ሳይሰለቹ እርሱን ተስቢሕ የሚያደርጉ መሆናቸውን ማመን ነው።
{አላህን ያዘዛቸውን ነገር (በመጣስ) አያምጹም፡፡ የሚታዘዙትንም ሁሉ ይሠራሉ።}
[ተሕሪም፡ 6]
ለእያንዳንዳቸው አላህ በእርሱ ላይ ግዴታ ያደረገበት ኃላፊነት አለባቸው። ከእነርሱም መካከል ዓርሽን ተሸካሚዎች አሉ፤ ከነርሱም ነፍስን የማውጣት ኃላፊነት የተጣለበት አለ፤ ከእነርሱም ከሰማይ የተወረደን ወሕይ (መለኮታዊ ራእይ) ይዞ የመውረድ ኃላፊነት ያለበት አለ ይሀውም ጂብሪል (የአላህ ሰላም በእርሱ ላይ ይሁን) ሲሆን ከመካከላቸው በላጩም እርሱው ነው። ከመካከላቸውም የጀነት ጠባቂና የጀሀነም ጠባቂ አሉ። ሌሎችም ደጋግ መላእክቶች አሉ። ከሰዎች መካከል ምእመናን የሆኑትንም ይወዷቸዋል፤ ለምእመናኖቹ ከአላህ መሀርታን መጠየቅንና ዱዓእ ማድረግንም ያበዛሉ።
ሦስተኛው ማዕዘን- ከአላህ በወረዱ ኪታቦች (መጽሐፍት) ማመን፦
በዚህም ሙስሊሙ አላህ ከመልክተኞቹ በሻው ላይ ጥራት ይገባውና ከእርሱ የሆኑ ትክክለኛ መረጃንና ፍትሃዊ መመርያዎችን የያዙ ኪታቦቹን (መጽሐፍት) ያወረደ መሆኑን ያምናል። በሙሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ተውራትን፣ በዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ኢንጅልን፣ በዳውድ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ዘቡርን እና በኢብራሂም (የአላህ ሰላም በእነርሱ ላይ ይሁን) ላይ ደግሞ ሱሑፍን አውርዷል። እነዚህ የተጠቀሱት ኪታቦች (መጽሐፍት) ታዲያ መጀመርያውኑ በወረዱበት ይዘት የሚገኙ አይደሉም። እንዲሁም በነብያቶቹ መደምደሚያ ሙሐመድም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ቁርአንን ማውረዱን እንደሚያምኑ ሁሉ ማለት ነው። አላህ ተከታታይ አንቀጾች ለሃያ ሶስት አመታት ያወረደ ሲሆን ለውጥና መዛባት እንዳያገኘውም ጠብቆታል።
{እኛ ቁርኣንን እኛው አወረድነው። እኛም ለእርሱ ጠባቂዎቹ ነን።}
[አል-ሒጅር: 9]
አራተኛው ማዕዘን፡ በመልዕክተኞች ማመን
(በርግጥ ስለነብያቶች ቀደም ብለን በዝርዝር አውርተናል) እናም በጥቅሉ በመላው የሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ላሉ ህዝቦች ሁሉ ሃይማኖታቸው አንድ አይነት አምላካቸውም አንድ የሆነ የሰው ዘር በሙሉ አንዱን አምላክ አላህን እንዲያመልክ፤ ከሽርክ፣ ከክህደትና አመፅም እንዲቆጠቡ በሚል መርህ ዳዕዋ የሚያደርጉ የሆኑ ነብያቶች ተልኮላቸዋል።
{ማንኛይቱም ሕዝብ በውስጧ አስፈራሪ ያላለፈባት የለችም።}
[ፋጢር፡ 24]
ነብያቶች አላህ መልእክቱን ለማስተላለፍ የመረጣቸው ከመሆናቸው ውጭ እንደሌሎች ሰዎች ሁሉ እነርሱም ሰዎች ናቸው።
{እኛ ወደ ኑሕና ከርሱ በኋላ ወደ ነበሩት ነቢያት እንዳወረድን ወደ አንተም አወረድን፡፡ ወደ ኢብራሂምም፣ ወደ ኢስማዒልም፣ ወደ ኢስሓቅም፣ ወደ ያዕቆብም፣ ወደ ነገዶቹም፣ ወደ ዒሳም፣ ወደ አዩብም፣ ወደ ዩኑስም፣ ወደ ሃሩንና፣ ወደ ሱለይማንም አወረድን። ለዳውድም ዘቡርን ሰጠነው።}
{ከዚህም በፊት በአንተ ላይ በእርግጥ የተረክናቸውን መልክተኞች ባንተ ላይም ያልተረክናቸውን መልክተኞች (እንደላክን ላክንህ)። አላህም ሙሳን ማነጋገርን አነጋገረው።}
{ከመልክተኞቹ በኋላ ለሰዎች በአላህ ላይ አስረጅ እንዳይኖር አብሳሪዎችና አስፈራሪዎች የኾኑን መልክተኞች (ላክን)። አላህም አሸናፊ ጥበበኛ ነው።}
[ኒሳእ: 163‐165]
ሙስሊሞች በሁሉም ነብያቶች ያምናሉ፤ ይወዷቸዋልም፤ ለሁሉም ደጋፊያቸውም ናቸው፤ በመካከላቸውም ልዩነትን አይፈጥሩም። በመሆኑም ከመነብያቶቹ በአንዳቸው እንኳ የካደ ወይም የዘለፋቸው አልያም ክብራቸውን ያጎደፈ ወይም ደግሞ አስቸጋሪ ሆኖ የተገኘ ሁሉ በሁሉም እንደካደ ነው።
ከመካከላቸውም በላጩና አላህ ዘንድም በማዕረግ ታላቁ የነብያት መደምደሚያ የሆኑት ነብዩ ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ናቸው።
አምስተኛው ማዕዘን፡ በመጨረሻው ቀን ማመን
አላህም ባሮቹን ከመቃብራቸው እንደሚቀሰቅሳቸው ሁሉንም በእለተ ትንሣኤ በቅርቢቱ ሕይወት ለሠሩት ሥራ ሊተሳሰባቸውም እንደሚሰበስባቸው ማመን ነው።
{ምድር በሌላ ምድር የምትለወጥበትን ሰማያትም (እንደዚሁ) አንድ አሸናፊ ለኾነው አላህም (ፍጡራን ሁሉ) የሚገለጹበት ቀን (አስታውሱ)።}
[ኢብራሂም: 48]
{ሰማይ በተሰነጠቀች ጊዜ፤}
{ከዋክብትም ተበታትነው በወደቁ ጊዜ፤}
{ባሕሮችም በተከፈቱና በተደበላለቁ ጊዜ፤}
{መቃብሮችም በተገለባበጡና (ሙታን) በተነሱ ጊዜ፤}
{ማንኛይቱም ነፍስ ያስቀደመችውንና ያቆየችውን ታውቃለች።}
[አል‐ኢንፊጧር: 1‐5]
{ሰውየው እኛ ከፍቶት ጠብታ የፈጠርነው መኾናችን አላወቀምን? ወዲያውም እርሱ (ትንሣኤን በመካድ) ግልጽ ተከራካሪ ይኾናልን?}
{ለእኛም ምሳሌን አደረገልን። መፈጠሩንም ረሳ። «አጥንቶችን እነርሱ የበሰበሱ ሲኾኑ ሕያው የሚያደርጋቸው ማነው?» አለ።}
{«ያ በመጀመሪያ ጊዜ (ከኢምንት) ያስገኛት ሕያው ያደርጋታል። እርሱም በፍጡሩ ሁሉ (ኹኔታ) ዐዋቂ ነው» በለው።}
{ያ ለእናንተ በእርጥብ ዛፍ እሳትን ያደረገላችሁ ነው። ወዲያውኑም እናንተ ከእርሱ ታቀጣጥላላችሁ።}
{ያ ሰማያትንና ምድርን የፈጠረ ብጤያቸውን በመፍጠር ላይ ቻይ አይደለምን? ነው እንጅ። እርሱም በብዙ ፈጣሪው ዐዋቂው ነው።}
{ነገሩም አንዳችን በሻ ጊዜ ኹን ማለት ነው። ወዲያው ይኾናልም።}
{ያ የነገሩ ሁሉ ስልጣን በእጁ የኾነው ጌታ ጥራት ይገባው። ወደእርሱም ትመለሳላችሁ።}
[ያሲን: 77‐83]
{በትንሣኤም ቀን ትክክለኛ ሚዛኖችን እናቆማለን። ማንኛይቱም ነፍስ ምንንም አትበደልም። (ሥራው) የሰናፍጭ ቅንጣት ያክል ቢኾንም እርሷን እናመጣታለን። ተቆጣጣሪዎችም በኛ በቃ።}
[አል-አንቢያእ 47]
{የብናኝ ክብደት ያክልም መልካምን የሠራ ሰው ያገኘዋል። (8) የብናኝ ክብደት ያክልም ክፉን የሠራ ሰው ያገኘዋል።}
[አዝ-ዘልዘላህ 7-8]
የጀሀነም ደጆች በእርሱ ላይ የአላህ ቁጣና ጥላቻ ላለበት ለአሳማሚ ቅጣቱም የተገባ ለሆነ ሰው የሚከፈቱ ሲሆን የጀነት በሮችም በጎ ሰሪ ለሆኑ ምእመናን ይከፈታሉ።
{መላእክትም ይህ ያ ትቀጠሩ የነበራችሁት ቀናችሁ ነው፤ እያሉ ይቀበሏቸዋል።}
[አልአንቢያእ፡ 103
{እነዚያ የካዱትም የተከፋፈሉ ጭፍሮች ኾነው ወደ ገሀነም ይንነዳሉ፡፡ በመጧትም ጊዜ ደጃፎችዋ ይከፈታሉ፡፡ ዘበኞችዋም «ከእናንተ የኾኑ መልክተኞች የጌታችሁን አንቀጾች በናንተ ላይ የሚያነቡላችሁ የዚህንም ቀን መገናኘት የሚያስጠነቅቋችሁ አልመጡዋ ችሁምን?» ይሏቸዋል፡፡ «የለም መጥተውናል፤ ግን የቅጣቲቱ ቃል በከሓዲዎች ላይ ተረጋገጠች» ይላሉ።}
{እነዚያም ጌታቸውን የፈሩት የተከፋፈሉ ጭፍሮች ኾነው ወደ ገነት ይንነዳሉ። በመጧትም ጊዜ ደጃፎችዋ የተከፈቱ ሲኾኑ ዘበኞችዋም ለእነርሱ «ሰላም በናንተ ላይ ይኹን። ተዋባችሁ። ዘውታሪዎች ኾናችሁ ግቧት» በሏቸው ጊዜ (ይገቧታል)።}
{«ምስጋና ለአላህ ለዚያ ተስፋ ቃሉን ለሞላልን። የገነትን ምድር በምንሻው ስፍራ የምንሰፍር ስንኾን ላወረሰን ይገባው» ይላሉም። የሠሪዎችም ምንዳ ምን ያምር!}
[ዙመር፡ 71_75]
ይህች ጀነት፤ ዓይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ በሰው ልብ ውል ብሎ የማያውቅን ፀጋ ያለባት ነች።
{ይሠሩትም በነበሩት ለመመንዳት ከዓይኖች መርጊያ ለእነርሱ የተደበቀላቸውን (ጸጋ) ማንኛይቱም ነፍስ አታውቅም።}
{አማኝ የሆነ ሰው አመጸኛ እንደ ሆነ ሰው ነውን? አይስተካከሉም።}
{እነዚያ ያመኑና መልካሞችን የሰሩማ ለእነርሱ ይሠሩት በነበሩት ምክንያት መስተንግዶ ሲሆኑ መኖሪያ ገነቶች አሏቸው።}
{እነዚያ ያመጹትማ፤ መኖሪያቸው እሳት ናት። ከእርሷ መውጣትን በፈለጉ ቁጥር በእርሷ ውስጥ ይመለሳሉ። ለእነርሱም «ያንን በእርሱ ታስተባብሉበት የነበራችሁትን የእሳት ቅጣት ቅመሱ» ይባላሉ።}
[ሰጅዳህ፡ 17_20]
{የዚያች ጥንቁቆቹ ተስፋ የተሰጧት ገነት ምስል በውስጧ ሺታው ከማይለውጥ ውሃ ወንዞች፣ ጣዕሙ ከማይለወጥ ወተትም ወንዞች፣ ለጠጪዎች ሁሉ ጣፋጭ ከኾነች የወይን ጠጅም ወንዞች ከተነጠረ ማርም ወንዞች አልሉባት። ለእነርሱም በውስጧ ከፍሬዎች ሁሉ (በያይነቱ) ከጌታቸው ምሕረትም አልላቸው። (በዚች ገነት ውስጥ ዘውታሪ የኾነ ሰው) እርሱ በእሳት ውስጥ ዘውታሪ እንደኾነ ሰው፣ ሞቃትንም ውሃ እንደተጋቱ፣ አንጀቶቻቸውንም ወዲያውኑ እንደቆራረጠው ነውን? (አይደለም)።}
[ሙሓመድ፡ 15]
{አላህን ፈሪዎቹ በእርግጥ በገነቶችና በጸጋ ውስጥ ናቸው።}
{ጌታቸው በሰጣቸው ጸጋ ተደሳቾች ኾነው (በገነት ውስጥ ናቸው)። የገሀነምንም ስቃይ ጌታቸው ጠበቃቸው።}
{«ትሠሩት በነበራችሁት ምክንያት ተደሳቾች ኾናችሁ ብሉ፤ ጠጡም፤» (ይባላሉ)።}
{በተደረደሩ አልጋዎች ላይ ተደጋፊዎች ኾነው (በገነት ይኖራሉ)። ዓይናማዎች በኾኑ ነጫጭ ሴቶችም እናጠናዳቸዋለን።}
[ጡር፡ 17_20]
አላህ ሁላችንንም የጀነት ሰዎች ያድርገን።
ስድስተኛው ማዕዘን፡ መልካምም ሆነ መጥፎ በአላህ ቀደር (ቅድመ ውሳኔ) መሆኑን ማመን
እያንዳንዱ የዓለም እንቅስቃሴ ባጠቃላይ ልዕለ ኃያል በሆነው አላህ የተጻፈ ውሳኔ ነው።
{በምድርም በነፍሶቻችሁም መከራ (ማንንም) አትነካም ሳንፈጥራት በፊት በመጽሐፍ የተመዘገበች ብትኾን እንጅ። ይህ በአላህ ላይ ገር ነው።}
[አልሓዲድ፡ 22]
{እኛ ሁሉን ነገር በልክ ፈጠርነው።}
[አል ቀመር፡ 49]
{አላህ በሰማይና በምድር ውስጥ ያለን ሁሉ በእርግጥ የሚያውቅ መኾኑን አታውቅምን ይህ በመጽሐፍ ውስጥ (የተመዘገበ) ነው። ይህ በአላህ ላይ ገር ነው።}
[አልሓጅ፡ 70]
እነኝህን ስድስቱ ማእዘናት አሟልቶ በትትክል ያመነባቸው ማንኛውም ሰው ሙእሚን ከሆኑ የአላህ ባሮች ይመደባል። ፍጥራታቱ ታዲያ በእምነት ደረጃ አንዱ ከሌላው ይለያያሉ። ከደረጃዎች ሁሉ ከፍተኛው የእምነት ደረጃ የኢሕሳን ደረጃ ሲሆን ይኸውም “አላህን አንተ ባታየው እንኳ እሱ ያይሀልና ልክ እንደምታየው ሆነህ ልታመልከው” ወደምትችልበት ደረጃ መድረስ ነው።
እነዚህ በጀነት ውስጥ በፊርደውስ ካሉ ደረጃዎች ታላላቆቹን ደረጃዎች በመጎናፀፍ የስኬት ባለቤት የሆኑ የፍጥረታቱ ምርጦች ናቸው።
[5] አል-ቡኻሪ 4777 ዘግበውታል።