4- የእስልምና ምሰሶዎች (ማዕዘናት)
እስልምና እያንዳንዱ ሙስሊም ሙስሊም ለመባል ሊከተላቸው የሚገቡ አምስት ዋና ዋና ማዕዘናት አሉት፡-
የመጀመሪያው ማዕዘን፦ ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ አምላክ አለመኖሩን እና ሙሐመድም የአላህ መልዕክተኛ ናቸው ብሎ መመስከር።
ይህች ወደ እስልምና ሀይማኖት የሚገባ ሰው ከፍ ብለን በገለፅነው መልኩ በሙሉ መልእክቷ በማመን እንዲህ በማለት የሚናገራት የመጀመርያ ቃሉ ነች፡- “አሽሃዱ አን ላ ኢላሃ ኢለሏህ ወአሽሃዱ አነ ሙሓመደን ዓብዱሏሂ ወረሱሉህ” (ትርጉሙም: ከአላህ በስተቀር በእውነት የሚመለክ ሌላ አምላክ እንደሌለ እመሰክራለሁ፤ ሙሐመድም የአላህ ባሪያውና መልእክተኛው መሆናቸውን እመሰክራለሁ ማለት ነው።)
አላህ አንድና ብቸኛ አምላክ፤ ያልወለደ ያልተወለደ መሆኑን፤ ለእርሱ ብጤ እንደሌለው ፤ እርሱ የሁሉም ፈጣሪ ሲሆን ከእርሱም ውጭ ያሉ ሁሉ ፍጡር እንደሆኑ እና እርሱ ብቻ ሊመለክ የሚገባው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ። በመሆኑም ከአላህም ውጭ አምላክ ከእርሱም ውጭ ጌታ የለም። ሙሐመድም (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሰማይ መለኮታዊ ራእይ የሚደርሳቸው (ወሕይ የሚወርድላቸው) አምላክ ትእዛዙንና ክልከላውን የሚያስተላልፍላቸው የአላህ ባርያና መልእክተኛ መሆናቸውንም ያምናሉ። ስለዚህም የተናገሩትን ማመን፣ ያዘዙትን መታዘዝ፣ የከለከሉትንና ያስጠነቀቁትን መራቅ ከእያንዳንዱ ሙስሊም የሚጠበቅ ግዴታ ነው።
ሁለተኛው ማዕዘን፡ ሰላትን በአግባቡ መስገድ
በሶላት ዋነኛ የባርያነት እና የአምልኮ መገለጫዎች ለኃያሉ አላህ ብቻ ተለይተው ይጎላሉ። በዚህም አንድ የአላህ አገልጋይ ባሪያ ራሱን ዝቅ አድርጎ ቆሞ የቁርኣን አንቀጾችን እያነበበ አላህንም በሁሉም አይነት ዚክርና ውዳሴ እያወሳ፤ እያጎበደደና በግንባሩም እየተደፋ እየሰገደ ጌታውን አላህን ያዋያል፤ ይማፀነዋልም ከታላቅ ችሮታውም ይለምነዋል። በመሆኑም ሶላት ማለት በባሪያውና በፈጠረው፣ ግልጽንም፣ ሚስጥራዊውንም ተጨባጩን ብሎም በሰጋጆች መካከል ያለውን መገለባበጥም ከሚያውቅለት ጌታው ጋር ያለ ቁርኝት ነው። ሶላት አላህ ባርያውን እንዲወደው፣ ወደ እርሱም እንዲቀርብ፣ ወዶም እንዲቀበልለት ታላቋ ሰበብ ነች። ለአላህ ከመገዛት ተንጠባርሮ ሶላትን በእብሪተኝነት የተወ ሰው አላህ ተቆጥቶበትና ረግሞት ከእስልምና ይወጣል።
መቆምንና ሱረቱል ፋቲሓን መቅራትን (ማንበብ) አጠቃልሎ በቀን አምስት ሶላቶችን መስገድ ግዴታ ነው።
«ቢስሚልላሂ‐ር‐ሯሕማኒ‐ር‐ሯሒም» [ትርጉሙም: በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው] (1)
«አልሓምዱ ሊልላሂ ረቢል ዓለሚን» (ትርጉሙም: ምስጋና ለዓለማት ጌታ ለአላህ የተገባው ነው) (2)
«አር‐ሯሕማኒ‐ር‐ሯሒም» (ትርጉሙም: እጅግ በጣም አዛኝ አዛኝ እጅግ በጣም ሩኅሩህ) (3)
«ማሊኪ የውሚ‐ድ‐ዲን» (ትርጉሙም: የፍርዱ ቀን ባለቤት) (4)
«ኢይያከ ነዕቡዱ ወኢይያከ ነሰተዒን» (አንተን ብቻ እንገዛለን አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምንሃለን) (5)
«ኢህዲና‐ስ‐ሲሯጦል ሙስተቂም» (ትርጉሙም: ቀጥተኛውን መንገድ ምራን) (6)
«ሲሯጦ‐ል‐ለዚነ አንዓምተ ዓለይሂም ቐይሪል መቕዱቢ ዓለይሂም ወለድዷሊን» (ትርጉሙም: የእነዚያ ፀጋህን የዋልክላቸውን ሰዎች መንገድ በነዚያ የተቆጣህባቸውን እና የተሳሳቱትንም አይደሉም።) (7)
[አል_ፋቲሓ፡ 1_7]
እንዲሁም የተወሰነ የቁርአን አንቀፆችን ማንበብ፤ ሩኩዕ (ማጎብደድ)፣ ሱጁድ (በግንባር መደፋት)፣ አላህን መማፀንና “አሏሁ አክበር” ብሎ አላህን ማላቅ፣ ሩኩዕ ላይ “ሱብሓነ ረቢየል ዓዚም” በማለት ሱጁድ ላይ ደግሞ “ሱብሓነ ረቢየል አዕላ” በማለት አላህን ማጥራትንም አካትታለች።
ሰጋጅ ሶላትን ከማከናወኑ በፊት አስቀድሞ አካሉም ልብሱም ይሁን የሚሰግድበት ቦታ ሁሉ ከነጃሳ (ሽንትና ሰገራ መሰል) መፅዳት፤ ፊቱንና ሁለት እጆቹን በማጠብ፣ ራሱ ላይ በማበስና ከዚያም ሁለት እግሮቹንም በማጠብ በውኃ ውዱእ ማድረግ አለበት።
(በባልና ሚስት ግብረ ስጋ ግንኙነት) ጀናባ ሆኖ ከነበረ ደግሞ መላ ሰውነቱን በመታጠብ መፀዳዳት አለበት።
ሐ‐ ሶስተኛው ማእዘን: ዘካ
ለድሆች እና ለሚስኪኖች እንዲሁም ሌሎች ለሚገባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሰጥተው ችግራቸውን ያቃልሉበት ዘንድ አላህ በሃብታሞች ላይ የደነገገው የተወሰነ የገንዘብ መጠን ነው። የገንዘቡ መጠን ከአጠቃላይ ሀብቱ ሁለት ነጥብ አምስት (2.5%) ከመቶ ነው። የሚሰጠውም ለሚገባቸው ሰዎች ነው።
ይህ ምሰሶ በህብረተሰቡ መካከል ፍቅር፣ መግባባት እና መተጋገዝን በመጨመር ገንዘብበ የሌላቸው ሰዎች ተመቻችተው በሚኖሩ ሃብታሙ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ከሚያሳድሩት ምቀኝነትና ቂምም በመታደግ ማህበራዊ ትብብርን የሚያሰራጭ ነው። ለኢኮኖሚ እድገት እና ብልጽግና እንዲሁም ገንዘብን በተስተካከለ አኳኃን ዝውውር እንዲኖረውና ወደ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ይሆን ዘንድ አይነተኛው ምክንያት ነው።
ይህ ዘካ በየትኛውም የገንዘብ አይነት ማለትም በብር፣ በእንስሳ፣ በአዝርእትና ፍራፍሬ እንዲሁም በገበያ ሸቀጦችም ላይ ሁሉ እንደየ አይነቱ በተለያየ መጠን ግዴታ ነው።
መ‐ አራተኛው ማእዘን: የረመዷንን ወር መፆም
ፆም: ከፀሃይ መውጣት ጀምሮ ፀሓይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ አላህን ለመገዛት በማሰብ ከምግብ፣ ከመጠጥና ከግብረስጋ ግንኙነት መታቀብ ነው።
አላህ እንዲፆም ያዘዘበት ወር የሆነው ወርሀ ረመዷን በጨረቃ ተኮር የጊዜ አቆጣጠር (በሂጅሪ) ዘጠነኛው ወር ነው። ይህ ወር ማለት አላህ በመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላይ ቁርአኑን ማውረድ የጀመረበት ወር ነው።
የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
{(እንድትጾሙ የተጻፈባችሁ) ያ በርሱ ውስጥ ለሰዎች መሪ ከቅን መንገድና (እውነትን ከውሸት) ከሚለዩም ገላጮች (አንቀጾች) ሲኾን ቁርኣን የተወረደበት የረመዳን ወር ነው፡፡ ከእናንተም ወሩን ያገኘ ሰው ይጹመው፡፡}
[አል-በቀራህ: 185]
ፆም ከሚያስገኛቸው ታላላቅ ፋይዳዎች መካከል ትዕግስትን መለማመድ እንዲሁም ተቅዋን (አላህን መፍራትን) እና የልብ እምነትን ማጠናከር ይገኝበታል። ምክንያቱም ጾም በአላህና በባርያው መካከል ያለ ምስጢራዊ ቁርኝት እንደመሆኑ መጠን ማንም ሰው ሳያውቅበት ከሰዎች ተደብቆ መብላትና መጠጣት እንደሚችል እያወቀ አላህን ለመገዛትና ትእዛዙንም ከመፈፀም አኳያ መታቀቡ ለአላህ ያለው ተቅዋ (ፍራቻ) እና እምነቱን እንዲጨምር ምክንያት ይሆንለታል። ስለዚህም ነው ፆመኞች አላህ ዘንድ ያላቸው ምንዳም ከፍ ከማለቱ በተጨማሪ በጀነት ውስጥ አር-ረያን የሚባል ልዩ በር የተመደበላቸው።
በተጨማሪም የትኛውም ሙስሊም በራሱ ፈቃድ ከወርሀ ረመዷን ውጭ በማንኛውም ወር የዓመቱን ቀናት የዒድ አል‐ፈጥርንና ዒድ አል‐አድሐን ሲቀር ሊፆም ይችላል።
ሠ – አምስተኛው ማዕዘን፡- ወደ ተቀደሰው ቤት ሐጅ ማድረግ
ሐጅ ማድረግ የሚችል የትኛውም ሙስሊም በህይወት ዘመኑ አንድ ጊዜ የመፈፀም ግዴታ ያለበት ሲሆን ከዛ በላይ የሚጨምር ከሆነ ደግሞ በውዴታው ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
“ለአላህም በሰዎች ላይ ወደርሱ መሄድን በቻለ ሁሉ ላይ ቤቱን መጎብኘት ግዴታ አለባቸው።”
[አሊ-ዒምራን 97]
ሓጅ በሚደረግባቸው ማለትም በሂጅሪ አቆጣጠር የመጨረሻዎቹ ወራት ሙስሊሙ በተከበረችዋ መካ ወደሚገኙ ልዩ የአምልኮ ቦታዎች የሚጓዝ ሲሆን ሙስሊሙ መካ ከመግባቱ በፊት ልብሶቹን አወላልቆ የኢሕራም ልብሱን ይለብሳል። ይህም እነዚያን በሞተ ጊዜ የሚለብሳቸውን ሁለት ነጫጭ ከፈኖች የሚጠቁም አንድምታ አላቸው።
ከዚያም የተለያዩ የሐጅ ሥራዎችን ማለትም በተከበረው ካዕባ ዙርያ ጠዋፍ ማድረግ፣ በሰፋ እና መርዋ መካከል መሮጥ፣ በአረፋ ሜዳ ላይ መቆም፣ በሙዝደሊፋ ማደር፣ ወዘተ ያከናውናል።
ሐጅ በምድር ላይ ካሉ የሙስሊሞች ስብስብ ትልቁ ሲሆን በመካከላቸውም ወንድማማችነት፣ መተዛዘንና መመካከርን ያሰፍናል። አለባበሳቸው አንድ አይነት፤ የአምልኮ ስርአታቸውም አንድ አይነት ነው። አንዳቸውም ከሌላው ለአላህ ካላቸው ፍራቻ (ተቅዋ) ካልሆነ በቀር አይበላለጡም። የሐጅ ስርአት ምንዳው ታላቅ ነው። ነቢዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ ብለዋል፡-
(ያለ ጸያፍ ድርጊትና ያለ አመፅ ሐጅ ያደረገ ልክ እናቱ እንደወለደችው ቀን ከኃጢአቱ ይጠራል።) [4]
[4] ሐዲሡን አል-ቡኻሪ (2/164) ኪታቡል ሐጅ: ፈድሉ አልሓጀል መብሩር በሚለው ባብ ስር ዘግበውታል።