የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

1- የተውሒድ ቃል (ላ ኢላሃ ኢለላህ)

የእስልምና ሀይማኖት መሰረታዊው ህገ መርህ ቃለ‐ተውሒድ (ላ ኢላሃ ኢለላህ) ነው። ይህ ጠንካራ መሰረት ከሌለ ከፍ ያለው የእስልምና ህንፃ ሊገነባ አይችልም። ወደ እስልምና ሀይማኖት የሚገባ ሰው በእርሱ አምኖበት በሁሉም ትርጉሞቹ እና ፍቺው አምኖበት ሊናገረው የሚገባ የመጀመሪያው ቃል ነው። ታዲያ “ላ ኢላሃ ኢለላህ” ማለት ምን ማለት ነው?

“ላኢላሃ ኢለሏህ” ማለት፦

ከአላህ በቀር ምንም ፈጣሪ የለም።

በዚህ ዓለም ውስጥ ከአላህ በቀር ባለቤትም ሆነ አስተናባሪ ምንም የለም።

ከአላህ በቀር አምልኮ የሚገባው አምላክ የለም።

ይህንን ሰፊ፣ ውብ፣ አምሳያ የለሽ የሆነውን ዩኒቨርስ የፈጠረው አላህ ነው። ይህች ሰማይ ካላት ድንቅ ከዋክብት እና በየምህዋራቸው በተራቀቀ ስርአት እና አስደናቂ እንቅስቃሴ የሚዞሩ ፕላኔቶች ጋ አላህ ብቻ ነው የሚይዛቸው። ይህች ምድር ተራሮችዋና ሸለቆዎችዋ፣ ኮረብቶችና ወንዞቿ፣ ዛፎቿና እርሻዎቿ፣ አየሯና ውኃዋ፣ የብሷና ባሕሯ፣ ሌሊትና ቀኗ፣ በውስጧ ከያዘቻቸው ነዋሪዎቿና የሚመላለስባትም ሁሉ አላህ ያላንዳች የፈጠራቸውና ያስገኛቸው የአላህ ፍጡራን ናቸው።

የላቀው አላህ በተከበረው ቁርኣን እንዲህ ብሏል፦

{ፀሐይም ለእርሷ ወደ ሆነው መርጊያ ትሮጣለች። ይህ የአሸናፊው የዐዋቂው አምላክ ውሳኔ ነው።}

{ጨረቃንም የመስፈሪያዎች ባለቤት ሲኾን እንደ ዘንባባ አሮጌ ቀንዘል እስኪኾን ድረስ (መኼዱን) ለካነው።}

{ፀሐይ ጨረቃን ልትደርስበት አይገባትም። ሌሊትም ቀንን (ያለ ጊዜው) ቀዳሚ አይኾንም። ሁሉም በመዞሪያቸው ውስጥ ይዋኛሉ።}

[ያሲን፡ 38_40]

{ምድርንም ዘረጋናት። በእርሷም ውስጥ ጋራዎችን ጣልንባት። በውስጧም ከሚያስደስት ዓይነት ሁሉ አበቀልን።}

{(ይህንን ያደረግነው) ተመላሽ ለኾነ ባሪያ ሁሉ ለማሳየትና ለማስገንዘብ ነው።}

{ከሰማይም ብሩክን ውሃ አወረድን። በእርሱም አትክልቶችንና የሚታጨድን (አዝመራ) ፍሬ አበቀልን።}

{ዘምባባንም ረዣዢም ለእርሷ የተደራረበ እንቡጥ ያላት ስትኾን (አበቀልን).}

[ቃፍ፡ 7_10]

ይህ ሁሉ ጥራት ይገባውና የልዑል ኃያሉ አላህ አፈጣጠር ነው። ምድርን መርጊያ አደረጋት፤ የመሬት ስበትንም ለህይወት በሚመጥን መልኩ አደረገላት፤ እላፊ ሄዶ በእርሷ ላይ ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ በሚሆንበት መልኩም ሳይሆን በውስጧ የያዘቻቸው ሕይወት ያላቸው ነገሮች እስኪበሩ ቀንሶም ሳይሆን የተመጠነ የመሬት ስበት አደረገላቸው። ሁሉም ነገር እርሱ ዘንድ በልክ ነው።

ከእርሱ ውጭ ህይወት የማትቆምበት የሆነውን ንጹሕ ውሃን ከሰማይ አወረደ።

{ሕያው የሆነንም ነገር ሁሉ ከውሃ ፈጠርን።}

[አል-አንቢያእ፡ 30]

በውኃውም እፅዋትና ፍራፍሬን አወጣ፤ እንስሳትንና ሰዎችንም አጠጣ፤ ምድሪቱንም ጠብቃ እንድታኖር አድርጎ አመቻቻትና ለምንጭነትና ወንዝነትም ገራት።

በዛውም ማራኪ ውበት ያላቸው ዛፎች፣ አበቦች፣ ጽጌረዳዎችን እና አትክልቶችን አበቀለ። ያ ሁሉንም ፍፁም አድርጎ የፈጠረው አምላክ የሰውን ፍጥረት ከጭቃ ጀመረው።

የመጀመርያው ሰው ሆነው የተፈጠሩት የሰው ልጆች ሁሉ አባት አደም ዓለይሂ ሰላም ሲሆኑ፥ ከጭቃ ነው የተፈጠሩት። ከዚያም አስተካከላቸው፣ ቀረፃቸውና ከነፍስም እስትንፋስን እፍ አለባቸው። ከዛም ጥንዳቸውን ከጎናቸው ፈጠረ። ከዚያም ዘራቸውን ከተንጣለለ ከደከመ ውኃ አደረገ።

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{በእርግጥም ሰውን ከነጠረ ጭቃ ፈጠርነው።}

{ከዚያም በተጠበቀ መርጊያ ውስጥ የፍትወት ጠብታ አደረግነው።}

{ከዚያም ጠብታዋን (በአርባ ቀን) የረጋ ደም አድርገን ፈጠርን። የረጋውንም ደም ቁራጭ ሥጋ አድርገን ፈጠርን። ቁራጯንም ሥጋ አጥንቶች አድርገን ፈጠርን። አጥንቶቹንም ሥጋን አለበስናቸው። ከዚያም (ነፍስን በመዝራት) ሌላ ፍጥረትን አድርገን አስገኘነው። ከሚቀርጹትም ሁሉ በላጭ የሆነው አላህ ላቀ።}

[አል-ሙእሚኑን: 12-14]

የላቀው አላህ እንዲህም ይላል፦

{(በማኅፀኖች) የምታፈሱትን አያችሁን?}

{እናንተ ትፈጥሩታላችሁን? ወይስ እኛ ፈጣሪዎቹን ነን?}

{እኛ ሞትን (ጊዜውን) በመካከላችሁ ወሰንን። እኛም ተሸናፊዎች አይደለንም።}

{ብጤዎቻችሁን (መሰላችሁን)በመለወጥና በዚያ በማታውቁትም (ቅርጽ) እናንተን በመፍጠር ላይ (አንሸነፍም)።}

[አል_ዋቂዓህ፡ 58_61]

እስኪ አላህ አንተን የፈጠረበትን የአፈጣጠር ስርአት አስተውል። አይደለም የመቆጣጠር ችሎታው ሊኖርህ ቀርቶ ስለ አሠራራቸው ራሱ ጥቂቱን እንጅ በማታውቀው መልኩ ባለ ረቂቅ መሳሪያዎች እና የተዋጣለት ስርዓቶችን ያቀፈ ድንቅ ሆኖ ታገኘዋለህ። ይህ የምግብ ውህደት ስርዓትን እስኪ ተመልከተው፥ እጅግ የተሟላ ስርዓት ነው። ምግቡን በቀላሉ ፈጭቶ ለማዋሀድ እንዲመች በትናንሽ ቁርጥራጮች መቆራረጡ ከአፍ ይጀመራል። ከዚያም ጉሮሮ ጉርሻውን ወደ ማንቁርት ይወረውረውና ሀብለ ድምፅ (እንጥል) የምግብ በርን ከፍቶ የመተንፈሻ ቱቦን ከዘጋው በኋላ ጉርሻው በምግብ ቱቦ በኩል ወደ አንጀት ይመዝገዘጋል።

በአንጀትም ውስጥ የምግብ ውህደት ሂደቱ ይቀጥላል። ምግቡም ወደ ፈሳሽነት ይለወጣል። ከዚያም በሆድ ውስጥ ያለው መግቢያ ቀዳዳ ይከፈትለትና የምግብ ውህደቱ የምግብ ጥሬ እቃው ለሰውነት የሚበጅ ወደሆነ ንጥረ ነገር ተለውጦ ሌላውን የሰውነት አካል ተስማሚ ይሆን ዘንድ ወደ ሴሎችም ያመራል።

ከዚያም የምግብ ውህደቱ ወደሚጠናቀቅበት ወደ ትንሹ አንጀት ያመራል። በዚህም ሁኔታ ምግቡ በአንጀት ውስጥ በሚገኘው ፀምረ አንጀት በመመጠጥ ከደም ዝውውር ጋር አብሮ ሊዘዋወር የሚመች ይሆናል።

ይህ በተወሳሰቡ ደም ወሳጅ ቧንቧዎች ውስጥ ለሚዘረጋው የደም ዝውውር የተቀናጀ ስልት ነው። እነሱን ብትለያቸውና ብትነጣጥላቸው ርዝመታቸው ወደ ሺዎች ኪሎ ሜትር የሚደርስ ነው። ልብ ከሚባል ማዕከላዊ የደም ቱቦ ጣቢያ ጋር የተገናኘ ነው። ይህም ጣቢያ ደሙን በደም ወሳጅ ቧንቧዎች በኩል ለማጓጓዝ የማይታክት የማይሰለች ነው።

ሌላ ደሞ የመተንፈሻ ስልት አለ። አራተኛም ነርቭ አለ፤ አምስተኛው ደግሞ የትርፍ ነገር ማውጫ አለ፤ እና ስድስተኛው፤ ሰባተኛው … አስረኛው እና በየእለቱ ይበልጥ እያወቅን የምንሄዳቸው ነገሮች ሁሉ አሉ። ይህም ሆኖ በውስጣችን ከምናውቀው ይልቅ የማናውቀው ይበዛል። ይህንን የሰው ልጅ እንዲህ በተራቀቀ መልኩ ከአላህ በቀር ማን ፈጠረው?!

ስለዚህም ነው ከኃጢአት ሁሉ የከፋው አላህ ፈጥሮህ ሳለ፥ ከአላህ ጋ ተጋሪ ማድረግህ የሆነው።

እስኪ በክፍት ልቦና እና ግልጽ (ቅን) በሆነ መንፈስ ሆነህ ዐይንን የሚያሳውር ቀለም ሳይኖረው ከየቦታው ሁሉ እየሳብክ ስለምትተነፍሰው አየር አስተውል፤ ለጥቂት ደቂቃዎች ቢቋረጥብህ ህይወትህም ቀጥ ብላ ትቆማለች ማለት እኮ ነው። ይህ የምትጠጣው ውሃ፣ ያ የምትበላው ምግብ፣ ይህ የምትወደው ሰው፣ የምትራመድባት ምድር፣ የምትመለከተው ሰማይ፣ ዓይንህ የሚያየውና የማያየው ትልቅም ይሁን ትንሽ ፍጡራን ሁሉ፣ ሁሉም ፈጣሪና አዋቂ ከሆነው አላህ ፍጥረታት ናቸው።

ስለ አላህ ፍጥረታት ማሰላሰል፥ የአላህን ታላቅነትን እና ኃያልነትን ያስገነዝበናል። እጅግ ከሚደንቁ ሞኞች፣ የድንቁርና እና የጥመት ሰዎች መካከል ይህንን እጅግ ልዩ፣ ታላቅ፣ የተቀናጀ እና ፍፁም የሆነ እንዲሁም አስደናቂ ጥበብና የላቀ ችሎታን አስረጅ የሆነ ፍጥረትን እየተመለከተ፥ ያላንዳች (አምሳያና አጋዥ) በፈጠራት ፈጣሪዋ የማያምን ከሃዲ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{ወይስ ያለ አንዳች (ፈጣሪ) ተፈጠሩን? ወይስ እነርሱ ፈጣሪዎች ናቸውን?}

{ወይስ ሰማያትንና ምድርን ፈጠሩን? አይደለም አያረጋግጡም።}

[አጥ-ጡር 35-36]

የትኛዋም ጤናማ አእምሮ መማር ሳያስፈልጋት የላቀውን ከፍ ያለውን አላህን ታወቀዋለች። ገና ከአፈጣጠሯ ጀምሮ ወደ እርሱ መቅጣጨትን እና መመለስን ፈጠሮላታል። ነገር ግን ከእርሱም የሚያጠማትና የሚያርቃት ነገር ይገጥማታል።

ስለዚህም እኮ ነው ጥፋት፣ ወረርሽኝ ወይም ከባድ ጭንቅና መከራ ሲገጥማት፣ እንዲሁም በምድርም ሆነ በባህር ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ሲጋረጣባት፣ ካለችበት ጭንቅ ለመገላገል፣ እርዳታን ለማግኘትና ለመትረፍ በቀጥታ መጠጊያዋን ወደ አላህ ነው የምታደርገው። እናም የላቀው አላህም ተጨንቀው ለሚማፀኑት መልስ ይሰጣል፤ ክፋትንም ያስወግዳል።

ይህ ታላቅ ፈጣሪ ከሁሉ የሚበልጥ ታላቅ ነው። እንደውም ፍጡራኑን ከእርሱ ጋ ፈጽሞ ማነፃፀር አይገባም፤ እርሱ ታላቅነቱ ወሰን የሌለውና ማንም በእውቀት ሊያካብበው የማይችል ታላቅ ነው። ከፍጥረታቱም በላይ ከሰማያትም በላይ መሆኑ መገለጫው ነው።

{የእርሱ አምሳያ ምንም የለም እርሱ ሰሚ ተመልካች ነው።}

[አሽ ሹራ፡ 11]

ከፍጥረታቱ ምንም አምሳያ የለውም፤ በአእምሮህ ውል ያለብህ ሁሉ ምንም ይሁን አላህ እንደዚያ አለመሆኑን እወቅ።

የላቀው (አላህ) ከሰማያት በላይ ሆኖ ያየናል እኛ ግን አናየውም።

{ዓይኖች አያገኙትም፤ (አያዩትም)። እርሱም ዓይኖችን ያያል። እርሱም ርኅራኄው ረቂቁ ውስጠ ዐዋቂው ነው።}

[አል_አንዓም፡ 103]

ይልቁንም ህዋሶቻችንም ይሁን ችሎታችን በዚህ ዓለም እርሱን ለማየት አቅሙ የላቸውም።

ይህንንም ከአላህ መልዕክተኞች መካከል አንዱ የሆኑት ሙሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይስፈን) አላህን በአጥ-ጡር ተራራ ላይ ሆኖ ሲያናግራቸው አላህን ለማየት ጠይቀው ነበር፡- “ጌታዬ ሆይ ወደ አንተ እንድመለከት አሳየኝ” አሉ። ከዚያም የላቀው አላህ እንዲህ አላቸው፦

{(አላህም)፡- «በፍጹም አታየኝም ግን ወደ ተራራው ተመልከት። በስፍራውም ቢረጋ በእርግጥ ታየኛለህ» አለው። ጌታው ለተራራው በተገለጸ ጊዜ እንኩትኩት አደረገው። ሙሳም ራሱን ስቶ ወደቀ። በአንሰራራም ጊዜ «የላቅከው ጌታ። ወዳንተ ተመለስኩ። እኔም (በወቅቱ) የምእምናን መጀመሪያ ነኝ» አለ።}

[አል_አዕራፍ፡ 143]

አላህ ለተራራው በመገለጡ፥ ታላቁና ከፍ ያለው ግኡዙ ተራራ ተንኮታኩቷል ተሰነጣጥቋል፤ ታዲያ ሰው እንዴት ነው በደካማ አቅሙ ማየት የሚችለው።

የላቀው አላህ ከመገለጫ ባህሪያቱ መካከል አንዱ እርሱ ነገሩን ሁሉ ማድረግ ቻይ መሆኑ ነው።

{አላህም በሰማያትም ሆነ በምድር ውስጥ ምንም ነገር የሚያቅተው አይደለም።}

[ፋጢር፡ 44]

ሕይወትና ሞት በእጁ ነው። ፍጡራን ሁሉ ከርሱ ፈላጊ ናቸው፤ እርሱ ከፍጡራኑ የተብቃቃ ነው። ከፍ ያለው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{እናንተ ሰዎች ሆይ! እናንተ (ሁል ጊዜ) ወደ አላህ ከጃዮች ናችሁ። አላህም እርሱ ተብቃቂው ምስጉኑ ነው።}

[ፋጢር፡ 15]

የላቀው አላህ ከባህሪያቱም መካከል ሁሉንም ነገር ያካበበ እውቀቱ ይገኝበታል።

{የሩቅ ነገርም መክፈቻዎች እርሱ ዘንድ ናቸው። ከእርሱ በቀር ማንም አያውቃቸውም። በየብስና በባሕር ያለውንም ሁሉ ያውቃል። ከቅጠልም አንዲትም አትረግፍም የሚያውቃት ቢኾን እንጅ። ከቅንጣትም በመሬት ጨለማዎች ውስጥ የለም ከእርጥብም ከደረቅም አንድም የለም ግልጽ በኾነው መጽሐፍ ውሰጥ (የተመዘገበ) ቢኾን እንጅ።}

[አል-አንዓም: 59]

አንደበታችን የሚናገረውንና አካሎቻችን የሚሠሩትን ብሎም ልቦናዎቻችን የሚደብቁትን ሁሉ ያውቃል።

{(አላህ) የዓይኖችን ክዳት ልቦችም የሚደብቁትን ሁሉ ያውቃል።}

[ጋፊር፡ 19]

የላቀው አላህ ስለኛ ሁሉን ነገር ያውቃል። ሁኔታዎቻችንንም ጠንቅቆ የሚያውቅ፤ በምድርም በሰማይም ምንም ነገር የማይሰወርበት፤ የማይዘነጋ፣ የማይረሳና የማይተኛ ነው።

{አላህ ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ የለም። ሕያው ራሱን ቻይ ነው። ማንገላጀትም እንቅልፍም አይዘውም። በሰማያት ውስጥና በምድር ውስጥ ያለው ሁሉ የርሱ ብቻ ነው። ያ እርሱ ዘንድ በፈቃዱ ቢኾን እንጅ የሚያማልድ ማነው? (ስለ ፍጡሮች) ከፊታቸው ያለውንና ከኋላቸው ያለውን ሁሉ ያውቃል። በሻውም ነገር እንጂ ከዕውቀቱ በምንም ነገር አያካብቡም (አያውቁም)። መንበሩ ሰማያትንና ምድርን ሰፋ። ጥበቃቸውም አያቅተውም። እርሱም የሁሉ በላይ ታላቅ ነው።}

[አል-በቀራህ: 255]

እንከን ወይም ነውር የሌለበት የተሟላ ፍጹምነት ባህሪ ባለቤት ነው።

እጅግ የተዋቡ ስሞች እና ምሉዕ ባህሪያት አሉት። የበላይ የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{ለአላህም መልካም ስሞች አሉት። (ስትጸልዩ) በእርሷም ጥሩት። እነዚያንም ስሞቹን የሚያጣምሙትን ተውዋቸው። ይሠሩት የነበሩትን ነገር በእርግጥ ይምመነዳሉ።}

[አል_አዕራፍ፡ 180]

የላቀው አላህ በግዛቱ (በንግስናው) ምንም ተጋሪ፣ አቻ ረዳት የለውም።

የላቀው (አላህ) ባለቤትና ልጅ ከመያዝም የላቀ ነው። ይልቁንም እርሱ ከዚህ ሁሉ የተብቃቃ ነው። የበላይ የሆነው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{«እርሱ አላህ አንድ ነው።በል}

{«አላህ (የሁሉ) መጠጊያ ነው።}

{«አልወለደም፤ አልተወለደምም።}

{«ለእርሱም አንድም ብጤ (አቻ እና መሳይ) የለውም።»}

[አል-ኢኽላስ 1-4]

የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{«አልረሕማንም ልጅን ያዘ (ወለደ)» አሉ።}

{ከባድ መጥፎን ነገር በእርግጥ አመጣችሁ።}

{ከእርሱ (ከንግግራቸው) ሰማያት ሊቀደዱ፣ ምድርም ልትሰነጠቅ፣ ጋራዎችም ተንደው ሊወድቁ ይቃረባሉ።}

{ለአልረሕማን ልጅ አልለው ስለአሉ።}

{ለአልረሕማን ልጅን መያዝ አይገባውም።}

{በሰማያትና በምድር ያለው ሁሉ (በትንሣኤ ቀን) ለአልራሕማን ባሪያ ኾነው የሚመጡ እንጂ ሌላ አይደሉም።}

[መርየም 88-93]

የላቀው (አላህ) በግርማ ሞገስ (ታላቅነት)፣ በውበት፣ በኃያልነት፣ በታላቅነት፣ በኩራት፣ በንግሥናና በመለኮት የሚገለጽ የላቀ ጌታ ነው።

የልግስና፣ የይቅር ባይነት፣ የእዝነት እና የቸርነት ባህሪያትም አሉት፤ እርሱ እዝነቱ ሁሉንም ነገር ያካተተ እጅግ መሐሪ ነው።

(አዛኝ) ርህራሄውም ቁጣውን የሚቀድም ርኅሩኅ ነው።

ልግስናው ገደብ የለሽ የሆነ ለጋስ፤ ካዝናውም ማለቂያ የሌለው ጌታ ነው።

ስሞቹ ሁሉ መልካምና ያማሩ ናቸው፤ ለአላህ ብቻ ካልሆነ በቀር ለሌላ የማይገቡ የሙሉዕነትና የፍፁምነት መገለጫ የሆኑት ባህሪያትንም ያመለክታሉ።

ጥራት የተገባውን አላህ፥ ባህሪያቱን ማወቅ፥ ልቦና ለእርሱ ያላትን ፍቅር፣ ማላቅ፣ ፍርሃትንና አክብሮትን ይጨምራል።

ስለዚህም “ላ ኢላሃ ኢለላህ” የሚለው ቃል ፍቺው ከአምልኮት የቱንም ቢሆን ከአላህ ውጭ ላለ አካል ስለማይሰጥ ከአላህ በቀር በእውነት አምልኮ የሚገባው የለም ነው። የአምላክነት እና የፍፁምነት ባህሪያት ያለው እርሱ ነውና። ፈጣሪ፣ ሲሳይ ለጋሽ፣ ፀጋ የሚሰጥ፣ ሕይወት ሰጪ፣ ሕይወት የሚነሳው፣ ለፍጡራኖቹ በጎ የሚውል እርሱው በመሆኑ ለአምልኮ የሚገባው ተጋሪ የሌለው ብቸኛ እርሱው ነው።

የአላህን መመለክ ያልፈለገ ወይም ከአላህ ሌላ የሚገዛ ሰው ሽርክንና ክህደትን ፈፅሟል።

ስለዚህም ሱጁድ መውረድ፣ ማጎብደድ፣ መዋረድ እና ሰላት ለአላህ ካልሆነ በቀር ለሌላ አይሆንም።

ወደ አላህ ካልሆነ በቀር የድረሱልኝ ዱዓ አይደረግም፤ ወደ አላህ እንጂ በዱዓእ አይዞርም፤ ከአላህም ካልሆነ በቀር ጉዳዮችን (እንዲፈጽምልን) አይከጀልም፤ መቃረቢያን፣ መታዘዝንና አምልኮንም ወደ አላህም ካልሆነ በቀር ላማንም አይደረግም።

«ስግደቴ፣ መገዛቴም፣ ሕይወቴም፣ ሞቴም ለዓለማት ጌታ ለአላህ ነው» በል።

«ለእርሱ ተጋሪ የለውም። በዚህም (በማላቅ) ታዘዝኩ። እኔም የሙስሊሞች መጀመሪያ ነኝ» (በል)።

[አል_አንዓም፥162_163]

About The Author

ምላሽ ይስጡ

ኢ-ፖስታ አድራሻወ ይፋ አይደረግም። መሞላት ያለባቸው መስኮች * ምልክት አላቸው