የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

ተ – ነቢዩ ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)

ንጽሕት የሆነችው የዒምራን ልጅ ድንግል መርየም ከሙሳ በኋላ በተላኩት ቅዱሳት መፃህፍት ያሉ መመርያዎችን በሚገባ የምትከተል ጥሩ የአላህ ባርያ እንዲሁም አላህ ከአለማት የመረጣቸው ቤተሰቦችም አባል ነበረች። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ በሚከተለው መልኩ እንዳለን፡-

{አላህ አደምን፣ ኑሕንም፣ የኢብራሂምንም ቤተሰብ፣ የዒምራንንም ቤተሰብ በዓለማት ላይ መረጠ።}

[አሊ-ዒምራን 33]

መላእክትም አላህ የመረጣት eንደሆነች አብስረዋታል፦

{መላእክትም ያሉትን (አስታውስ)። «መርየም ሆይ! አላህ በእርግጥ መረጠሸ። አነጻሽም። በዓለማት ሴቶችም ላይ መረጠሽ።»}

{«መርየም ሆይ! ለጌታሽ ታዘዢ። ስገጂም። ከአጎንባሾቹም ጋር አጎንብሺ።»}

[አሊ-ዒምራን 42_43]

ከዚያም ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ ዒሳን በማህፀኗ ውስጥ ያለ አባት እንዴት እንደፈጠረውም በሚከተለው ቃሉ አሳወቀን፦

{በመጽሐፉ ውስጥ መርየምንም ከቤተሰቧ ወደ ምሥራቃዊ ስፍራ በተለይች ጊዜ (የሆነውን ታሪኳን) አውሳ።}

{ከእነሱም መጋረጃን አደረገች። መንፈሳችንምም (ጂብሪልን) ወደርሷ ላክን። ለእርሷም ትክክለኛ ሰው ሆኖ ተመሰለላት።}

{«እኔ ከአንተ በአልረሕማን እጠበቃለሁ። ጌታህን ፈሪ እንደ ሆንክ (አትቅረበኝ)» አለች።}

{«እኔ ንጹሕን ልጅ ለአንቺ ልሰጥሽ የጌታሽ መልክተኛ ነኝ» አላት።}

{«(በጋብቻ) ሰው ያልነካኝ ሆኜ አመንዝራም ሳልሆን ለእኔ እንዴት ልጅ ይኖረኛል!» አለች።}

{አላት «(ነገሩ) እንደዚህሽ ነው።» ጌታሽ «እርሱ በእኔ ላይ ገር ነው። ለሰዎችም ታምር ከእኛም ችሮታ ልናደርገው (ይህንን ሠራን) የተፈረደም ነገር ነው» አለ፤ (ነፋባትም)።}

{ወዲያውኑም አረገዘችው። በእርሱም (በሆዷ ይዛው) ወደ ሩቅ ስፍራ ገለል አለች።}

{ምጡም ወደ ዘንባባይቱ ግንድ አስጠጋት። «ዋ ምኞቴ! ምነው ከዚህ በፊት በሞትኩ። ተረስቼም የቀረሁ በሆንኩ» አለች።}

{ከበታቿም እንዲህ ሲል ጠራት «አትዘኝ። ጌታሽ ከበታችሽ ትንሽን ወንዝ በእርግጥ አድርጓል።}

{«የዘምባባይቱንም ግንድ ወዳንቺ ወዝውዣት ባንቺ ላይ የበሰለን የተምር እሸት ታረግፍልሻለችና።}

{«ብይም፣ ጠጭም፣ ተደሰችም። እኔ ለአልረሕማን ዝምታን ተስያለሁ፤ ዛሬም ሰውን በፍጹም አላነጋግርም» በይ።}

{በእርሱም የተሸከመቺው ሆና ወደ ዘመዶቿ መጣች። «መርየም ሆይ! ከባድን ነገር በእርግጥ ሠራሽ» አሏት።}

{«የሃሩን እኅት ሆይ! አባትሽ መጥፎ ሰው አልነበረም። እናትሽም አመንዝራ አልነበረችም» አሏት።}

{ወደርሱም ጠቀሰች። «በአንቀልባ ያለን ሕጻን እንዴት እናናግራለን!» አሉ።}

{(ሕፃኑም) አለ «እኔ የአላህ ባሪያ ነኝ። መጽሐፍን ሰጥቶኛል ነቢይም አድርጎኛል።»}

{«በየትም ስፍራ ብሆን ብሩክ አድርጎኛል። በሕይወትም እስካለሁ ሶላትን በመስገድ ዘካንም በመስጠት አዞኛል።»}

{«ለእናቴም ታዛዥ (አድርጎኛል)። ትዕቢተኛ እምቢተኛም አላደረገኝም።}

{«ሰላምም በእኔ ላይ ነው። በተወለድሁ ቀን፣ በምሞትበትም ቀን፣ ሕያው ኾኜ በምቀሰቀስበትም ቀን።»}

{ይህ የመርየም ልጅ ዒሳ ነው። ያ በርሱ የሚጠራጠሩበት እውነተኛ ቃል ነው።}

{ለአላህ ልጅን መያዝ አይገባውም። (ከጉድለት ሁሉ) ጠራ። ነገርን በሻ ጊዜ ለርሱ የሚለው «ኹን» ነው ወዲያውም ይኾናል።}

{(ዒሳ አለ) «አላህም ጌታዬ ጌታችሁም ነውና ተገዙት። ይህ ቀጥተኛ መንገድ ነው።»}

[መርየም፡ 16-36]

ከዚያም ነብዩሏህ ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሰዎችን አላህን እንዲያመልኩ ጥሪ (ዳዕዋ) ሲያደርጉላቸው ብዙዎች ጀርባቸውን ቢሰጡም ጥሪያቸውን የተቀበሉም ግን ነበሩ። እርሳቸውም አምላኬ አምላካችሁ አላህን አምልኩ የሚለው ዳዕዋቸውን ቀጠሉ፤ ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ዳዕዋውን አስተባበሉ፤ ጭራሽ አሴሩባቸውና እስከመግደል ሙከራም ደረሱ! የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{ዒሳ ሆይ! እኔ ወሳጂህ ወደ እኔም አንሺህ ነኝ፡፡ ከነዚያም ከካዱት ሰዎች አጥሪህ ነኝ}

[አሊ-ዒምራን 55]

በዚህም አላህ ዒሳን እያሳደዷቸው ከነበሩት መካከል በአንዱ ላይ የዒሳን ምስል ጣለበትና የመርየም ልጅ ዒሳን እያሰቡ ባልንጀራቸውን ቀፈደዱትም ሰቅለው ገደሉትም። የአላህ መልዕክተኛ ዒሳን ግን አላህ ወደ ሰማይ አንስቷቸዋልና አልደረሱባቸውም። በዚህ መልኩ ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ዱኒያን ለቀው ከማረጋቸው በፊት ሃይማኖቱን የሚያሰራጭ አሕመድ የተባለን አፅናኝ መልዕክተኛ አላህ እንደሚልክ ለባልደረቦቹ ነግሯቸው ነበር። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦

{የመርየም ልጅ ዒሳም፡- «የእስራኤል ልጆች ሆይ! እኔ ከተውራት በፊቴ ያለውን የማረጋግጥና ከእኔ በኋላ በሚመጣው መልክተኛ ስሙ አሕመድ በኾነው የማበስር ስኾን ወደእናንተ (የተላክሁ) የአላህ መልክተኛ ነኝ» ባለ ጊዜ (አስታውስ)። በግልጽ ተዓምራቶች በመጣቸውም ጊዜ «ይህ ግልጽ ድግምት ነው» አሉ።}

[አስ_ሶፍ፡ 6]

ከዚያም የዒሳ ተከታዮችን እስከመከፋፈል ያደረሳቸው ጊዜ መጣች። በዚህም ዒሳን የአላህ ‐ጥራት ይገባውና‐ ልጅ ነው የሚል አንጃ እስከመፈጠር ደረሰ። የዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ያለ አባት መወለድም ለዚህ ጥመታቸው መታለያ ሆናቸው። የላቀው አላህ ይህን በማስመልከት በተከታዩ ቃሉ እንዲህ ብሏል፦

{አላህ ዘንድ የዒሳ ምሳሌ እንደ አዳም ብጤ ነው። ከዐፈር ፈጠረው። ከዚያም ለርሱ (ሰው) «ሁን» አለው፤ ሆነም።}

[አሊ-ዒምራን 59]

የዒሳ ዓለይሂ ሰላም ያለ አባት መፈጠር ከአዳም ያለ አባትም ያለ እናትም ከመፈጠር በላይ የሚደንቅ አይደለም።

ስለዚህም ነበር የላቀው አላህ በቁርኣን ውስጥ ለእስራኤል ልጆች ከዚህ የክህደት ቃል ሊርቁ ዘንድ እንዲህ በማለት ያነጋገራቸው፦

{እናንተ የመጽሐፉ ሰዎች ሆይ! በሃይማኖታችሁ ወሰንን አትለፉ። በአላህም ላይ እውነትን እንጅ አትናገሩ። የመርየም ልጅ አልመሲሕ ዒሳ የአላህ መልክተኛ ወደ መርየም የጣላት «የኹን» ቃሉም ከእርሱ የኾነ መንፈስም ብቻ ነው። በአላህና በመልክተኞቹም እመኑ። « (አማልክት) ሦስት ናቸው» አትበሉም። ተከልከሉ፤ ለእናንተ የተሻለ ይኾናልና። አላህ አንድ አምላክ ብቻ ነው። ለእርሱ ልጅ ያለው ከመኾን የጠራ ነው። በሰማያትና በምድር ያለ ሁሉ የርሱ ነው። መመኪያም በአላህ በቃ።}

{አልመሲሕ (ኢየሱስ) ለአላህ ባሪያ ከመኾን ፈጽሞ አይጠየፍም። ቀራቢዎች የኾኑት መላእክትም (አይጠየፉም)። እርሱን ከመገዛት የሚጠየፍና የሚኮራም ሰው (አላህ) ሁሉንም ወደ እርሱ በእርግጥ ይሰበስባቸዋል።}

{እነዚያማ ያመኑት መልካሞችንም የሠሩት ምንዳዎቻቸውን ይሞላላቸዋል። ከችሮታውም ይጨምርላቸዋል። እነዚያን የተጠየፉትንና የኮሩትንማ አሳማሚን ቅጣት ይቀጣቸዋል። ከአላህም ሌላ ለእነሱ ዝምድንና ረዳትን አያገኙም።}

[አን_ኒሳእ፡ 171_173]

አላህ የቂያማ እለት ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እንዲህ በማለት ያነጋግራቸዋል፦

{አላህም፡- «የመርየም ልጅ ዒሳ ሆይ! አንተ ለሰዎቹ፡- እኔንና እናቴን ከአላህ ሌላ ሁለት አምላኮች አድርጋችሁ ያዙ ብላሃልን» በሚለው ጊዜ (አስታውስ)። «ጥራት ይገባህ፤ ለእኔ ተገቢዬ ያልኾነን ነገር ማለት ለኔ አይገባኝም። ብዬው እንደ ኾነም በእርግጥ ዐውቀኸዋል። በነፍሴ ውስጥ ያለውን ሁሉ ታውቃለህ። ግን አንተ ዘንድ ያለውን አላውቅም። አንተ ሩቆችን ሁሉ በጣም ዐዋቂ አንተ ብቻ ነህና» ይላል።}

{«በእርሱ ያዘዝከኝን ቃል ጌታዬንና ጌታችሁን አላህን ተገዙ ማለትን እንጂ ለነርሱ ሌላ አላልኩም። በውስጣቸውም እስካለሁ ድረስ በነርሱ ላይ ተጣባበቂ ነበርኩ። በተሞላኸኝም ጊዜ (ባነሳኸኝ ጊዜ) አንተ በነሱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ። አንተም በነገሩ ሁሉ ላይ ዐዋቂ ነህ።»}

{«ብትቀጣቸው እነርሱ ባሮችህ ናቸው። ለነርሱ ብትምርም አንተ አሸናፊው ጥበበኛው ነህ።» (ይላል)።}

{አላህም ይላል፡- «ይህ እውነተኞችን እውነታቸው የሚጠቅምበት ቀን ነው። ለእነርሱ በሥሮቻቸው ወንዞች የሚፈሱባቸው በውስጣቸው ሁልጊዜ ዘውታሪዎች ሲኾኑ የሚኖሩባቸው ገነቶች አሉዋቸው። አላህ ከእነሱ ወደደ፤ እነርሱም ከእርሱ ወደዱ፤ ይህ ታላቅ ዕድል ነው።»}

[አል-ማኢዳህ 116-119]

በመሆኑም የመርየም ልጅ ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው ከሰየሙትና ራሳቸውን የነብዩ ዒሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ተከታዮች አድርገው ከሚቆጥሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የጠሩ ናቸው።

About The Author