የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

ቀ – ነቢዩ ሹዐይብ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)

ከዚያም አላህ ሰዎቹ ከጠመሙና በመካከላቸውም መጥፎ ስነምግባር፣ በሰዎች ላይ ግፈኝነት፣ በልኬት (ስፍር) እና ሚዛን ላይ ማዛባት ከተንሰራፋ በኋላ ለመድየን ህዝቦች ወንድማቸው ሹዓይብን ላከላቸው። ስለ እነሱም አላህ እንዲህ ሲል ነግሮናል፡-

{ወደ መድየንም (ምድያን) ወንድማቸውን ሹዓይብን (ላክን)፤ አላቸው፡- «ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ከእርሱ በቀር ምንም አምላክ የላችሁም። ከጌታችሁ ዘንድ ግልጽ ማስረጃ በእርግጥ መጥታላችኋለች። ስፍርንና ሚዛንን ሙሉ። ሰዎችንም አንዳቾቻቸውን (ገንዘቦቻቸውን) አታጉድሉባቸው። በምድርም ውስጥ ከተበጀች በኋላ አታበላሹ። ይህ ምእምናን እንደኾናችሁ ለእናንተ የተሻለ ነው።»}

{« (ሰዎችን) የምታስፈራሩና ከአላህም መንገድ በእርሱ ያመኑትን የምታግዱ መጥመሟንም የምትፈልጉዋት ኾናችሁ በየመንገዱ አትቀመጡ። ጥቂቶችም በነበራችሁና ባበዛችሁ ጊዜ አስታውሱ። የአጥፊዎችም መጨረሻ እንዴት እንደነበረ ተመልከቱ።»}

{«ከእናንተም በዚያ እኔ በእርሱ በተላክሁበት ያመኑ ጭፍሮችና ያላመኑ ጭፍሮችም ቢኖሩ በመካከላችን አላህ እስከሚፈርድ ታገሱ። እርሱም ከፈራጆች ሁሉ በላጭ ነው።»}

{ከሕዝቦቹ እነዚያ የኮሩት መሪዎች፡- «ሹዓይብ ሆይ! አንተንና እነዚያን ከአንተጋር ያመኑትን ከከተማችን በእርግጥ እናስወጣችኋለን። ወይም ወደ ሃይማኖታችን መመለስ አለባችሁ አሉ። የጠላንም ብንኾን» አላቸው።}

{«አላህ ከእርሷ ከአዳነን በኋላ ወደ ሃይማኖታችሁ ብንመለስ በአላህ ላይ በእርግጥ ውሸትን ቀጠፍን። አላህ ጌታችን ካልሻም በስተቀር ለእኛ ወደእርሷ ልንመለስ አይገባንም። ጌታችን ዕውቀቱ ሁሉን ነገር ሰፋ። በአላህ ላይ ተጠጋን። ጌታችን ሆይ! በኛና በወገኖቻችን መካከል በውነት ፍረድ። አንተም ከፈራጆቹ ሁሉ በላጭ ነህ» (አለ)።}

{ከወገኖቹም እነዚያ የካዱት መሪዎች «ሹዓይብን ብትከተሉ እናንተ ያን ጊዜ ከሳሪዎች ናችሁ» አሉ።}

{ወዲያውም የምድር መንቀጥቀጥ (ጩኸትም) ያዘቻቸው። በቤቶቻቸውም ውስጥ ተንከፍርረው አነጉ።}

{እነዚያ ሹዓይብን ያሰተባበሉት በእርሷ እንዳልነበሩባት ኾኑ። እነዚ ሹዓይብን ያስተባበሉት እነርሱ ከሳሪዎች ኾኑ።}

{ከእነርሱም (ትቷቸው) ዞረ፡- «ወገኖቼ ሆይ! የጌታዬን መልክቶች በእርግጥ አደረስኩላችሁ። ለእናንተም መከርኩ። ታዲያ በከሓዲዎች ሰዎች ላይ እንዴት አዝናለሁ።» አለም።}

[አል-አዕራፍ፡ 85-93]

About The Author