ሸ – ነቢዩ ሉጥ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ከዚያም በኋላ አላህ ሉጥን ወደ ወገኖቹ ላከ እነርሱም ከአላህ ውጭም የሚያመልኩ በመካከላቸውም ዝሙትን የሚፈጽሙ ክፉ ሰዎች ነበሩ። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፦
{ሉጥንም ለሕዝቦቹ ባለ ጊዜ (አስታውስ)። «አስቀያሚን ሥራ ትሠራላችሁን በእርሷ ከዓለማት አንድም አልቀደማችሁም።»}
{«እናንተ ከሴቶች ሌላ ወንዶችን በመከጀል በእርግጥ ትመጡባቸዋላችሁ። በእውነቱ እናንተ ወሰንን አላፊዎች ሕዝቦች ናችሁ።»}
{የሕዝቦቹም መልስ « (ሎጥንና ተከታዮቹን) ከከተማችሁ አውጧቸው። እነሱ የሚጥራሩ ሰዎች ናቸውና» ማለት እንጂ ሌላ አልነበረም።}
[አል-አዕራፍ: 80-82]
አላህ እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከከሀዲዎች ወገን ከሆነችው ሚስቱ በስተቀር አዳናቸው። ይኸውም አላህ እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከመንደሩ እንዲወጡ በማዘዝ ነው። የአላህ ትእዛዝ በመጣማ ጊዜ የላይኛውን ዘቅዝቆ ወደ ታች ገለበጠው፤ ተከታታይ የሆነን የሸክላ ድንጋይም አዘነበባቸው።