ረ – ነቢዩ ሷሊሕ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ከዚያም የተወሰኑ ጊዜያቶች አለፉና ከአረብ ባህረ ገብ በስተ ሰሜን በኩል ባለ አካባቢ የሰሙድ ማህበረሰብ ተነሥተው እነዚያ ከእነሱ በፊት የነበሩት እንደጠመሙት እነርሱም ከመመሪያው ጠመሙ። አላህም ከእነሱ መካከል የሆነ (ሷሊህ) (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የተባሉ መልእክተኛን ወደ እነርሱ ላከላቸው፤ እውነተኛ የአላህ መልዕክተኝነታቸውን በሚያመለክቱ ተአምራትም አጠናከራቸው፤ ይኸውም ከፍጡራን ጋር አምሳያ የሌላት በሆነችው ታላቅ ግመል ነበር። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ በዚህ መልኩ ታሪኩን ነግሮናል፡-
{ወደ ሰሙድም ወንድማቸውን ሷሊህን ላክን። አላቸው «ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ከእርሱ ሌላ ለእናንተ ምንም አምላክ የላችሁም። (እውነተኛ ለመኾኔ) ከጌታችሁ የኾነች ምልክት በእርግጥ መጥታላችኋለች። ይህች ለእናንተ ተዓምር ስትኾን የአላህ ግመል ናትና ተዋት። በአላህ ምድር ውስጥ ትብላ፤ (ትጠጣም)። በክፉ አትንኳትም። አሳማሚ ቅጣት ይይዛችኋልና።»}
{«ከዓድም በኋላ ምትኮች ባደረጋችሁና በምድሪቱም ላይ ባስቀመጣችሁ ጊዜ አስታውሱ። ከሜዳዎቿ (ሸክላ) ሕንጻዎችን ትገነባላችሁ። ከተራራዎችም ቤቶችን ትጠርባላችሁ። ስለዚህ የአላህን ጸጋዎች አስታውሱ። በምድርም ውስጥ አጥፊዎች ኾናችሁ አታበላሹ።»}
{ከወገኖቹ እነዚያ የኮሩት መሪዎች ለእነዚያ ለተሸነፉት ከነሱ ላመኑት፡- «ሷሊህ ከጌታው መላኩን ታውቃላችሁን» አሏቸው። « (አዎን)፡- እኛ እርሱ በተላከበት ነገር አማኞች ነን» አሉ።}
{እነዚያ የኮሩት፡- «እኛ በዚያ እናንተ በርሱ ባመናችሁበት ከሓዲዎች ነን» አሉ።}
{ወዲያውም ግመሊቱን ወጓት። ከጌታቸውም ትዕዛዝ ወጡ። አሉም፡- «ሷሊህ ሆይ! ከመልክተኞቹ እንደኾንክ የምታስፈራራብንን (ቅጣት) አምጣብን።»}
{ወዲያውም የምድር መንቀጥቀጥ (ጩኸትም) ያዘቻቸው። በቤቶቻቸውም ውስጥ ተንከፍርረው አነጉ።}
{(ሷሊህ) ከእነርሱም ዞረ። (እንዲህም) አለ «ወገኖቼ ሆይ! የጌታዬን መልክት በእርግጥ አደረስኩላችሁ። ለእናንተም መከርኳችሁ። ግን መካሪዎችን አትወዱም።»}
[አል-አዕራፍ፡ 73-79]
ከዚህም በኋላ አላህ ብዙ መልክተኞችን ወደ ምድር ሕዝቦች ላከ። በውስጧ አስጠንቃቂ መልዕክተኛ ያላሳለፈች ሕዝብም አልነበረችም። አላህ ስለ ጥቂቶቹ የነገረን ቢሆንም ያልነገረን ብዙዎችም አሉ። ሁሉም ታዲያ አንድ መልእክት ብቻ ነው ለህዝባቸው ያስተላለፉት፤ ይኸውም ሰዎች ተጋሪ ሳያደርጉለት በብቸኝነት አላህን እንዲያመልኩ እና ከአላህ ውጪ ያለ አምልኮን እርግፍ አድርገው እንዲተዉ ማዘዝ ነው። የላቀው አላህ እንዲህ ብሏል፡
{በየሕዝቡም ሁሉ ውስጥ «አላህን ተገዙ፤ ጣዖትንም ራቁ» በማለት መልክተኛን በእርግጥ ልከናል። ከእነሱም ውስጥ አላህ ያቀናው ሰው አልለ። ከእነሱም ውስጥ በእርሱ ላይ ጥመት የተረጋገጠበት ሰው አልለ። በምድርም ላይ ኺዱ፤ የአስተባባዮችም መጨረሻ እንዴት እንደ ነበረ ተመልከቱ።}