መ – ነቢዩ ሁድ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ከዚያም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ አላህ አሕቃፍ በምትባል አካባቢ ወደሚኖሩ ዓድ ነገድ ማህበረሰብ ‐ጠምመው ከአላህ ውጭ ማምለክ በጀመሩ ጊዜ – ከእነሱ የሆኑትን ሁድ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መልእክተኛ አድርጎ ላከላቸው።
ይህንንም በማስመልከት የላቀው አላህ በሚከተለው መልኩ ነግሮናል፦
{ወደ ዓድም ወንድማቸውን ሁድን ላክን። «ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ከእርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም። (የአላህን ቅጣት) አትፈሩምን» አላቸው።}
{ከሕዝቦቹ እነዚያ የካዱት መሪዎች «እኛ በሞኝነት ላይ ኾነህ በእርግጥ እናይሃለን። እኛም ከውሸተኞቹ ነህ ብለን እንጠረጥርሃለን» አሉት።}
{(እርሱም) አላቸው «ወገኖቼ ሆይ! እኔ ሞኝነት የለብኝም። ግን እኔ ከዓለማት ጌታ የተላክሁ ነኝ።»}
{«የጌታዬን መልክቶች አደርስላችኋለሁ። እኔም ለእናንተ ታማኝ መካሪ ነኝ።»}
{«ከጌታችሁ የኾነ ግሣጼ ከእናንተው ውስጥ ባንድ ሰው ላይ ያስጠነቀቃችሁ ዘንድ ቢመጣባችሁ ትደነቃላችሁን ከኑሕም ሕዝቦች በኋላ ምትኮች ባደረጋችሁና በፍጠረትም ግዙፍነትን በጨመረላችሁ ጊዜ አስታውሱ። የሻችሁትንም ታገኙ ዘንድ የአላህን ጸጋዎች አስታውሱ።»}
{«አላህን ብቻውን እንድንገዛ አባቶቻችንም ይገዙት የነበረውን (አማልክት) እንድንተው መጣህብን ከውነተኞች ከኾንክ የምታስፈራብንን (ቅጣት) አምጣብን» አሉ።}
{«ከጌታችሁ የኾነ ቅጣትና ቁጣ በእናንተ ላይ በእውነት ተረጋገጠ። እናንተና አባቶቻችሁም (አማልክት ብላችሁ) በጠራችኋቸው ስሞች አላህ በእርሷ ምንም ማስረጃ ያላወረደባት ስትኾን ትከራከሩኛላችሁን ተጠባባቁም እኔ ከእናንተ ጋር ከተጠባባቂዎቹ ነኝና» አለ።}
{እርሱንና እነዚያንም አብረውት የነበሩትን ከእኛ በኾነው ችሮታ (ከቅጣት) አዳንናቸው። የእነዚያንም በተአምራታችን ያስተባበሉትንና አማኞች ያልነበሩትን መሠረት ቆረጥን።}
[አል-አዕራፍ፡ 65-72]
አላህም በእነሱ ላይ ለስምንት ቀናት ውስጥ በጌታዋም ፍቃድ ሁሉንም ነገር በምታጠፋ በሆነች የምትንሿሿ ብርቱ ነፋስን ላከባቸው፤ ነብዩሏህ ሁድ(የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና እነዚያን ከእርሳቸው ጋር ያመኑትን አላህ አዳናቸው።