የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

መ – ሙስሊሞች ይህንን ሃይማኖት በትትክል እንዲሰራጭ የሰጡት ትኩረት፦

የአላህ መልእክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ንግግር፣ ድርጊትና ማፅደቅ የአላህን ቃል፣ የእስልምና ሃይማኖት ትእዛዛት እና ክልከላዎችን የሚያብራሩና ግልፅ የሚያደርጉ ማስረጃዎች በመሆናቸው ሙስሊሞች እነዚህን ትውፊቶች (ሓዲሥ) ከመልዕክተኛው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) በመልቀሙ ላይም ይሁን የተዘገቡት ሐዲሶች በትክክል ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) የተገኙና ጭማሪ የሌላቸው የነጠሩ ሓዲሦች መሆናቸውን በማጣራቱም ላይ እንዲሁም ተድበስብሰው ሰርገው የገቡ ቅጥፈቶችን በማበጠሩ ላይም ታላቅ ትግልን አድርገዋል። ለዚህም ይረዳቸው ዘንድ እነዚህ ትውፊቶች ወይም ሓዲሦች ከተውልድ ትውልድ በሚተላለፉበት ጊዜ ሊስተዋሉ የሚገባቸውን ረቂቅ መርሆዎችንና ስርአትን አደረጉ።

እናም ለአንባቢ ምንም እንኳ ጊዜያቶች ቢነጉዱም አላህ ለዚች ሙስሊም ማህበረሰብ ያገራላት ስለሆነው ዲኗን ጥርት ንጥር ባለ መልኩ ውሸትና እንቶ ፈንቶ ሳይቀላቀልበት የነብያቸውን ተውፊቶችና ሓዲሦችን ከትውልድ ትውልድ ስላሸጋገሩበት ብሎም ከሌላው ጎዳናና ኡማ የተለዩበት ስለሆነው በዚህ የእውቀት ዘርፍ (የሐዲስ ጥናት) ዙርያ እጅግ ባጠረ መልኩ እንነጋገራለን።

የአላህ እና የመልዕክተኛውን (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አስተምህሮትና ንግግር መተላለፍ በሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው።

እነሱም በልቦና መሸምደድ እና በፅሁፍ ማስቀመጥ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ ሙስሊሞች ትክክለኛ የመሃፈዝ ችሎታና አስፍቶ የመገንዘብ ችሎታ ነበራቸው። ይህም የሚለዩበት በሆነው አእምሯዊ ጥራት እና የማስታወስ ብርታት አማካኝነት ነው። ይህ ደግሞ ታሪካቸውን ላጠና ስለ እነርሱ ለሚያውቅ ሰው ሁሉ የማይሰወርበትና ግልፅ የሆነ ጉዳይ ነው። ሶሓብዩ ከነብዩ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አንደበት ሓዲሥን ሰምቶ በደንብ ሸምድዶ ለቀጣዩ የመሸምደድ ችሎታ ያለው ታቢዒይ ያስተላልፋል። እርሱም በተራው ከሱ በኋላ ለነበሩት ያስተላልፈዋል። በዚህ ሂደት ሐዲሶችን ወደሚጽፍ አንድ የሐዲሥ ሊቅ ዘንድ እስኪደርስ ይቀጥልና ይህ ሊቅ በፅሁፍ ያሰፍረዋል። በልቦናውም ሸምድዶ በመፅሃፍ ውስጥም ያሰፍረውና ለተማሪዎቹም ይህንን መጽሐፍ ያነብላቸዋል። እነርሱም ሓዲሦቹን በቃላቸውም ሓፍዘው በፅሁፍም ያሰፍሩታል። ከዚያም እነርሱም ለተማሪዎቻቸው በዛው ሂደት ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፉታል። በዚህ መልኩና ሂደት (የዘገባ ሰንሰለት) እነዚህ የሓዲሥ ስብስቦች ወደ መላው ትውልድ እየተላለፉ ይገኛል።

በዚህም ምክንያት የትኛውም የረሱል (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሓዲሥ ዘገባው የተላለፈበት ሰንሰለት ሳይጣራ ሓዲሡ ተቀባይነትን አያገኝም።

ይህም የእስልምናን ማህበረሰብ ከሌሎች ማህበረሰቦች የሚለይበት የሆነን ሌላ እውቀት ይዞ መጣ። ይህም የዘገባ ሰንሰለት (ሰነድ) ጥናት ወይም የሰዎች ሓዲሥን ለማስተላለፍ ብቁ መሆንና አለመሆን የሚጣራበት የእውቀት ዘርፍ (ዒልመል ጀርሕ ወተዕዲል) ነው።

የአላህ መልእክተኛ ሰ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሓዲሥን ስለሚያስተላልፉ ዘጋቢዎች ማንነት የሚያጠና የእውቀት ዘርፍ ነው። በሓዲሡ ዘገባ ላይ ያሉ ግለሰቦች በነፍስ ወከፍ ደረጃ የሕይወት ታሪካቸውን፣ የተወለዱበትን እና የሞቱበትን ቀን፣ ሸይኾቻቸውና (መምህሮቻቸው) ተማሪዎቻቸው እነማን እንደነበሩ፣ የዘመኑ ሊቃውንት ዘንድ የነበራቸው የታማኝነት ደረጃ፣ የመሓፈዝ (የመሸምደድ) አቅምና ችሎታቸው፣ አደራ ጠባቂነትና የንግግራቸው እውነተኛነት እንዲሁም መሰል ማንነታቸውን የሓዲሥ አስተላላፊ ሊኖረው ከሚገባው ስብእና አኳያ የሚጠናበት የእውቀት ዘርፍ ነው።

ይህ እውቀት ህዝበ ሙስሊሙ ከነብያቸው (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ተላልፈዋል የተባሉ ሓዲሦችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ከሌላው ማህበረሰብ ሁሉ የተለዩበት እውቀት ነው። እናም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ያንድን አካል ንግግር ትክክለኛነት በማጣራት ረገድ ይህን የአላህ መልዕክተኛ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ንግግርን ለማጣራታ የተደረገውን ያህል ትልቅ እና ከፍተኛ ጥረት የተደረገበት የታሪክ ክስተት ተከስቶ አያውቅም።

በሓዲስ ዘገባ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ባደረጉ መፃህፍት የተሰበሰበ ትልቅ እውቀት ነው። እናም እነዚህ መጻሕፍት የረሱል (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሓዲሦችን ከትውልድ ወደ ትውልድ በማስተላለፍ ላይ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ብቻ የብዙ ሰዎችን የህይወት ታሪክ መዝግበዋል። በነዚህ የጥናቱ መፃህፍት ላይ እንደሚዛን የተቀመጡትን ረቂቅ መርሆችን ከመከተል ውጭ በጅምላ ፍረጃ አግበስብሶ ማለፍ የለም። የሚዋሸውን ይዋሻል ነው የሚባለው፤ ለእውነተኛውም እውነተኛ ነው፤ የሽምደዳ ችሎታው ደካማው ደካማ ነው፤ የሽምደዳ ችሎታ ጠንካራ የሆነውን ጠንካራ ሓፊዝ ነው ብለው ለዚህም ያመቻቸው ዘንድ የዘርፉ ሊቃውንት የሚያውቋቸው የሆኑ ረቂቅ መርሆዎችን አስቀምጠዋል።

እናም በዘርፉ ሊቆች መሰረት የሐዲሥ ዘጋቢዎች ሰንሰለት(ሰነድ) እርስ በርሱ የተቀጣጠለ ካልሆነ በቀር ሐዲሱ ሶሒሕ አይደለም። የተቀጣጠለው የሓዲሥ ዘገባ ሰንሰለትም (ሰነድ) ታዲያ እያንዳንዱ ዘጋቢ ለማስተላለፍ የሚያስቸለው ብቁነት፣ የንግግር እውነተኝነት ከጠንካራ የሽምደዳ ችሎታ ጋር ያሟላ ሊሆን ይገባዋል።

About The Author