የእስልምና ሃይማኖት

ቁርኣን እና ከሰዎች ሁሉ ምርጥ የሆኑት ነብይ ሓዲሦች እንደገለፁት

ለ – ከመልክተኞች የመጀመሪያው የሆኑት አባታችን አደም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)፡-

አላህ አባታችንን አደም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ከሸክላ ፈጥሯቸው ከዚያም ከነፍሱ (አላህ ከፈጠራቸው ነፍሶች መካከል አንዱን) እፍ አለባቸው። ልእለ ኋያሉ አላህ እንዲህ ብሏል፦

{በእርግጥም ፈጠርናችሁ። ከዚያም ቀረጽናችሁ። ከዚያም ለመላእክቶች «ለአዳም ስገዱ» አልን። ወዲያውም ሰገዱ። ኢብሊስ (ዲያብሎስ) ሲቀር ከሰጋጆቹ አልሆነም።}

{(አላህ) «ባዘዝኩህ ጊዜ ከመስገድ ምን ከለከለህ» አለው። «እኔ ከርሱ የበለጥኩ ነኝ። ከእሳት ፈጠርከኝ። እርሱን ግን ከጭቃ ፈጠርከው» አለ።}

{ከእርሷ ውረድ፤ በእርሷ ውስጥ ልትኮራ አይገባህምና። ውጣም አንተ ከወራዶቹ ነህና አለው።}

{«እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ አቆየኝ» አለ።}

{አንተ ከሚቆዩት ነህም አለው።}

[አል_አዕራፍ፡ 10_15

አላህ ጊዜ እንዲሰጠውና በቅጣትም እንዳያጣድፈው እንዲሁም ከምቀኝነቱና ከጥላቻውም አንፃር አዳምንና ዝርያውንም እንዲፈትናቸው እንዲፈቅድለት አላህን ተማፀነ። ከዚያም አላህ ለፈለገው ጥበብ ሲል ቅን ከሆኑ የአላህ ባርያዎች በስተቀር ሰይጣን በአደምና በዘሮቹ ላይ የማጥመም ሴራውን እንዲያደርግ ፈቀደ። አላህም አደምንና ልጆቹን ሰይጣንን እንዳያመልኩ ለፈተናውም እጅ እንዳይሰጡ ከሴራውም ለመከለል ወደ አላህ እንዲጠጉ አዘዛቸው። ሰይጣንም በአደምና በሚስታቸው ሐዋእ (አላህ ከጎኑ የጎድን አጥንት ከፈጠራት አካሉ) ላይ የመጀመሪያ ፈተናውን ጀመረ። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህ በቁርአን እንዳወሳው ማለት ነው።

{«አዳም ሆይ! አንተም ሚስትህም በገነት ተቀመጡ። ከሻችሁትም ስፍራ ብሉ። ግን ይህችን ዛፍ አትቅረቡ። (ራሳቸውን) ከሚበድሉት ትኾናላችሁና» (አላቸው)።}

{ሰይጣንም ከነውራቸው የተሸሸገውን ለእነርሱ ሊገልጽባቸው በድብቅ ንግግር ጎተጎታቸው። «ጌታችሁም መልኣኮች እንዳትኾኑ ወይም ከዘላለም ነዋሪዎች እንዳትኾኑ እንጂ ከዚህች ዛፍ አልከለከላችሁም» አላቸው።}

{«እኔ ለእናንተ በእርግጥ ከሚመክሩዋችሁ ነኝ» ሲልም አማለላቸው።}

{በማታለልም አዋረዳቸው። ከዛፊቱም በቀመሱ ጊዜ ኀፍረተ ገላቸው ለሁለቱም ተገለጠችላቸው። ከገነት ቅጠልም በላያቸው ላይ ይደርቱ ጀመር። ጌታቸውም «ከዚህ ዛፍ አልከለከልኋችሁምን ሰይጣንም ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነው አላልኳችሁምን» ሲል ጠራቸው።}

{«ጌታችን ሆይ! ነፍሶቻችንን በደልን። ለእኛ ባትምር ባታዝንልንም በእርግጥ ከከሳሪዎቹ እንኾናለን» አሉ።}

{(አላህ) « ከፊላችሁ ለከፊሉ ጠላት ሲኾን ውረዱ። ለእናንተም በምድር ላይ እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ መርጊያና መጠቀሚያ አላችሁ» አላቸው።}

{«በእርሷ ላይ ትኖራላችሁ። በእርሷም ላይ ትሞታላችሁ። ከእርሷም ውስጥ ትወጣላችሁ» አላቸው።}

{የአዳም ልጆች ሆይ! ኀፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን። አላህን የመፍራትም ልብስ ይህ የተሻለ ነው። ይህ ከአላህ ታምራቶች ነው። ይገሠጹ ዘንድ (አወረደላቸው)።}

{የአዳም ልጆች ሆይ! ሰይጣን አባትና እናታችሁን ኀፍረተ ገላቸውን ሊያሳያቸው ልብሶቻቸውን ከነሱ የገፈፋቸው ሲኾን ከገነት እንዳወጣቸው ሁሉ እናንተን አይሞክራችሁ። እነሆ እርሱ ከነሰራዊቱ ከማታዩዋቸው ስፍራ ያዩዋችኋልና። እኛ ሰይጣናትን ለእነዚያ ለማያምኑት ወዳጆች አድርገናል።}

[አል_አዕራፍ፡ 19_27]

አደም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ወደ ምድር ወርደው ልጆችንና ዘርን ከተለገሱ በኋላ ሞቱ። ከዚያም ዘራቸው ከትውልድ ትውልድ እየበዙ ሲሄዱ ለሰይጣን ፈተና ተዳረጉና መለያየት፣ የደጋግ አባቶቻቸውን ቀብር አምልኮ በመካከላቸው ተንሰራፋ፤ በአላህ ከማመን በአላህ ወደ ማጋራት ተዘዋወሩ፤ አላህም ነብዩሏህ ኑሕ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) መልዕክተኛ አድርጎ ላከ።

ሐ- ኑሕ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)፡-

በእርሳቸውና በአደም መካከል አሥር ክፍለ ዘመናት ነበሩ። አላህም ኑሕን ወደ ጠመሙትና ከአላህ ውጭ ጣኦታትን ማምለክ ወደ ጀመሩት ህዝቦቸው ላካቸው። ግኡዝ አካላትን፣ ድንጋይን፣ መቃብሮችንም ያመልኩ ነበር። እጅግ ገናና ከሆኑ ጣኦቶቻቸው መካከል ወድ፣ ሱዋዕ፣ የጉስ፣ የዑቅ እና ነስር የሚባሉ ነበሩ። አላህም ለአላህ ብቻ አምልኮ እንዲያደርጉ ያዟቸው ዘንድ ኑሕ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ላካቸው። ልክ የላቀው አላህ በተከታዩ የቁርአን አናቅፅ እንደነገረን ማለት ነው፦

{ኑሕን ወደ ወገኖቹ በእርግጥ ላክነው። አላቸውም፡- «ወገኖቼ ሆይ! አላህን ተገዙ። ለእናንተ ከርሱ ሌላ ምንም አምላክ የላችሁም። እኔ በእናንተ ላይ የከባድ ቀንን ቅጣት እፈራላችኋለሁ።»}

[አልአዕራፍ 59]

ህዝባቸውን አላህን ብቻ እንዲያመልኩ ጥሪ በማድረጉ ላይ ለረጅም ጊዜ ቀጠሉ። ይሁን እንጅ ከእርሳቸው ጋር ጥቂት ብቻ ነበሩ ያመኑት። ስለዚህም ኑሕ ጌታቸውን እንዲህ ሲሉ ተጣሩ፦

{(ስለ ተቃወሙትም) «አለ ጌታዬ ሆይ! እኔ ሌሊትም ቀንም ሕዝቦቼን ጠራሁ።}

{«ጥሪየም መሸሽን እንጅ ሌላ አልጨመረላቸውም።}

{«እኔም ለእነርሱ ትምር ዘንድ (ወደ እምነት) በጠራኋቸው ቁጥር ጣቶቻቸውን በጆሮዎቻቸው ውስጥ አደረጉ። ልብሶቻቸውንም ተከናነቡ። (በመጥፎ ሥራቸው ላይ) ዘወተሩም። (ያለ ልክ) መኩራትንም ኮሩ።}

{«ከዚያም እኔ በጩኸት ጠራኋቸው።}

{«ከዚያም እኔ ለእነርሱ ገለጽኩ። ለእነርሱም መመስጠርን መሰጠርኩ}

{«አልኳቸውም፡- ጌታችሁን ምሕረትን ለምኑት። እርሱ በጣም መሐሪ ነውና።}

{«በእናንተ ላይ ዝናምን ተከታታይ አድርጎ ይልካል።}

{«በገንዘቦችና በልጆችም ይለግሰላችኋል። ለእናንተም አትክልቶችን ያደርግላችኋል። ለእናንተም ወንዞችን ያደርግላችኋል።»}

{ለአላህ ልቅናን የማትሹት ለእናንተ ምን አላችሁ?}

{በልዩ ልዩ ኹኔታዎች በእርግጥ የፈጠራችሁ ሲኾን።}

About The Author