በ – ነቢዩ ሙሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን)
ያን ጊዜ አምላክ ነኝ ባይ የሆነው ፊርዓውን የተባለ ጨካኝና ትዕቢተኛ፤ ሰዎች እንዲሰግዱለት የሚያዝ፤ ያሻውን እያረደ ያሻውን የሚጨቁን ንጉስ ተነሳ። ጥራት ይገባውና የላቀው አላህም ስለ እርሱ እንዲህ ሲል ነግሮናል፦
{ፈርዖን በምድር ላይ ተንበጣረረ። ነዋሪዎቿንም የተከፋፈሉ ጓዶች አደረጋቸው። ከእነርሱ ጭፍሮችን ያዳክማል። ወንዶች ልጆቻቸውን በብዛት ያርዳል። ሴቶቻቸውንም ይተዋል፤ እርሱ ከሚያበላሹት ሰዎች ነበርና።}
{በእነዚያም በምድር ውስጥ በተጨቆኑ ላይ ልንለግስ፣ መሪዎችም ልናደርጋቸው ወራሾችም ልናደርጋቸው እንሻለን።}
{ለእነርሱም በምድር ላይ ልናስመች ፈርዖንንና ሃማንንም ሰራዊቶቻቸውንም ከእነሱ ይፈሩት የነበሩትን ነገር ልናሳያቸው (እንሻለን)።}
{ወደ ሙሳም እናት «አጥቢው፣ በርሱም ላይ በፈራሽ ጊዜ በባሕሩ ውስጥ ጣይው አትፈሪም፣ አትዘኝም፣ እኛ ወዳንቺ መላሾቹና ከመልክተኞቹም አድራጊዎቹ ነንና» ማለትን አመለከትን።}
{የፈርዖን ቤተሰቦችም (መጨረሻው) ለእነርሱ ጠላት ሐዘንም ይሆን ዘንድ አነሱት። ፈርዖንና ሃማንም ሰራዊቶቻቸውም ሀጢአተኞች ነበሩ።}
{የፈርዖንም ሚስት «ለእኔ የዓይኔ መርጊያ ነው። ለአንተም አትግደሉት ሊጠቅመን ወይም ልጅ አድርገን ልንይዘው ይከጀላልና» አለች። እነርሱም (ፍጻሜውን) የማያውቁ ሆነው (አነሱት)።}
{የሙሳም እናት ልብ ባዶ ሆነ። ከምእምናን ትሆን ዘንድ በልቧ ላይ ባላጠነከርን ኖሮ ልትገልጸው ቀርባ ነበር።}
{ለእኅቱም ተከታተይው አለቻት። እርሱንም እነሱ የማያውቁ ሲሆኑ በሩቅ ሆና አየችው።}
{(ወደናቱ ከመመለሱ) በፊትም አጥቢዎችን (መጥባትን) በእርሱ ላይ እርም አደረግን። (እኅቱ) «ለእናንተ የሚያሳድጉላችሁን እነርሱም ለእርሱ ቅን አገልጋዮች የሆኑን ቤተሰቦች ላመልክታችሁን» አለችም።}
{ወደእናቱም ዓይንዋ እንድትረጋ፣ እንዳታዝንም፣ የአላህም የተስፋ ቃል እርግጥ መሆኑን እንድታውቅ መለስነው። ግን አብዛኞቻቸው አያውቁም።}
{ብርታቱንም በደረሰና በተስተካከለ ጊዜ ጥበብንና ዕውቀትን ሰጠነው። እንዲሁም መልካም ሠሪዎችን እንመነዳለን።}
{ከተማይቱንም ሰዎቿ በዝንጋቴ ጊዜ ላይ ሆነው ሳሉ ገባ። በእርሷም ውስጥ የሚጋደሉን ሁለት ሰዎችን አገኘ። ይህ ከወገኑ ነው፤ ይህም ከጠላቱ ነው። ያም ከወገኑ የሆነው ሰው በዚያ ከጠላቱ በሆነው ሰው ላይ እርዳታን ጠየቀው። ሙሳም በጡጫ መታው። ገደለውም። ይህ ከሰይጣን ሥራ ነው። እርሱ ግልጽ አሳሳች ጠላት ነውና አለ።}
{«ጌታዬ ሆይ! እኔ ነፍሴን በደልኩ። ለእኔም ማር አለ።» ለእርሱም ምሕረት አደረገለት እርሱ መሓሪ አዛኝ ነውና።}
{«ጌታዬ ሆይ! በእኔ ላይ በመለገስህ ይሁንብኝ (ከስህተቴ እጸጸታለሁ)፤ ለአመጸኞችም ፈጽሞ ረዳት አልሆንም አለ።}
{በከተማይቱም ውስጥ ፈሪ የሚጠባበቅ ሆኖ አደረ። በድንገትም ያ ትላንት እርዳታን የጠየቀው ሰው በጩኸት እርዳታን ይጠይቀዋል። ሙሳ ለርሱ «አንተ በእርግጥ ግልጽ ጠማማ ነህ» አለው።}
{(ሙሳ) ያንን እርሱ ለሁለቱም ጠላት የሆነውን ሰው በኃይል ሊይዘው በፈለገም ጊዜ «ሙሳ ሆይ! በትላንትናው ቀን ነፍስን እንደ ገደልክ ልትገድለኝ ትፈልጋለህን በምድር ለይ ጨካኝ መሆንን እንጅ ሌላ አትፈልግም፡፡ ከመልካም ሠሪዎችም መሆንን አትፈልግም» አለው።}
{ከከተማይቱም ዳርቻ አንድ ሰው እየሮጠ መጣ። «ሙሳ ሆይ! ሹማምንቶቹ ሊገድሉህ ባንተ ይመካከራሉና ውጣ። እኔ ላንተ ከመካሪዎች ነኝና» አለው።}
{የፈራና የሚጠባበቅ ሆኖም ከእርሷ ወጣ። «ጌታዬ ሆይ! ከበደለኞቹ ሕዝቦች አድነኝ» አለ።}
{ወደ መድየን አቅጣጫ ፊቱን ባዞረ ጊዜም «ጌታዬ ቀጥተኛውን መንገድ ሊመራኝ እከጅላለሁ» አለ።}
{ወደ መድየንም ውሃ በመጣ ጊዜ በእርሱ ላይ ከሰዎች ጭፍሮችን (መንጋዎቻቸውን) የሚያጠጡ ሆነው አገኘ። ከእነርሱ በታችም (ከውሃው መንጎቻቸውን) የሚከለክሉን ሁለት ሴቶች አገኘ። «ነገራችሁ ምንድን ነው» አላቸው። «እረኞቹ ሁሉ (መንጋዎቻቸውን) እስከሚመልሱ አናጠጣም። አባታችንም ትልቅ ሽማግሌ ነው» አሉት።}
{ለሁለቱም አጠጣላቸው። ከዚያም ወደ ጥላው ዘወር አለ። «ጌታዬ ሆይ! እኔ ከመልካም ነገር ወደኔ ለምታወርደው ፈላጊ ነኝ» አለ።}
{ከሁለቱ አንደኛይቱም ከሐፍረት ጋር የምትኼድ ሆና መጣችው። «አባቴ ለእኛ ያጠጣህልንን ዋጋ ሊሰጥህ ይጠራሃል» አለችው። ወደእርሱ በመጣና ወሬውን በእርሱ ላይ በተረከለትም ጊዜ «አትፍራ ከበደለኞቹ ሕዝቦች ድነሃል» አለው።}
{ከሁለቱ አንደኛይቱም «አባቴ ሆይ ቅጠረው። ከቀጠርከው ሰው ሁሉ በላጩ ብርቱው ታማኙ ነውና» አለችው።}
{«ስምንትን ዓመታት ልታገለግለኝ እኔ ከእነዚህ ሁለት ሴቶቸ ልጆቼ አንዲቱን ላጋባህ እሻለሁ። ዐስርን ብትሞላም ከአንተ ነው። ባንተ ላይ ማስቸገርንም አልሻም። አላህ የሻ እንደ ኾነ ከመልካሞቹ ሰዎች ኾኜ ታገኘኛለህ» አለው።}
{(ሙሳም) «ይህ (ውለታ) በእኔና ባንተ መካከል (ረጊ) ነው። ከሁለቱ ጊዜያቶች ማንኛውንም ብፈጽም በእኔ ላይ ወሰን ማለፍ የለም። አላህም በምንለነው ላይ ምስክር» ነው አለ።}
{ሙሳም ጊዜውን በጨረሰና ከቤተሰቦቹ ጋር በኼደ ጊዜ ከጡር ተራራ ጎን እሳትን አየ። ለቤተሰቡ (እዚህ) «ቆዩ እኔ እሳትን አየሁ። ከእርሷ ወሬን ወይም ትሞቁ ዘንድ ከእሳት ትንታግን አመጣላችኋለሁ» አለ።}
{በመጣትም ጊዜ ከሸለቆው ቀኝ ዳርቻ ከዛፊቱ በኩል በተባረከችው ስፍራ ውስጥ «ሙሳ ሆይ! እኔ የዓለማት ጌታ አላህ እኔ ነኝ» በማለት ተጠራ።}
{«በትርህንም ጣል» (ተባለ)። እንደ ትንሽ እባብ ስትስለከለክ ባያትም ጊዜ ወደ ኋላ ዞሮ ሸሸ፤ አልተመለሰምም። «ሙሳ ሆይ! ተመለስ አትፍራም፤ አንተ ከጥብቆቹ ነህና» (ተባለም)።}
{«እጅህን በአንገትጌህ ውስጥ አግባ። ያለ ነውር ነጭ ሆና ትወጣለችና። ክንፍህንም ከፍርሃት (ለመዳን) ወዳንተ አጣብቅ። እነዚህም ከጌታህ የሆኑ ወደ ፈርዖንና ወደ መኳንንቶቹ የሚደርሱ ሁለት አስረጅዎች ናቸው። እነርሱ አመጸኞች ሕዝቦች ነበሩና።»}
{(ሙሳ) አለ «ጌታዬ ሆይ! እኔ ከእነርሱ ነፍስን ገድያለሁ። ስለዚህ እንዳይገድሉኝ እፈራለሁ።}
{«ወንድሜም ሃሩን እርሱ ምላሱ ከእኔ የተባ ነው። እውነተኛነቴንም የሚያረጋግጥልኝ ረዳት ኾኖ ከእኔ ጋር ላከው። እኔ ሊያስተባብሉኝ እፈራለሁና።»}
{(አላህም) «ጡንቻህን በወንድምህ በእርግጥ እናበረታለን። ለሁለታችሁም ስልጣንን እናደርጋለን። ወደእናንተም (በመጥፎ) አይደርሱም። በተዓምራቶቻችን (ኺዱ)። እናንተና የተከተላችሁም ሁሉ አሸናፊዎች ናችሁ» አላቸው።}
[አልቀሶስ፡ 4-35]
[1] እናታቸው በሣጥኑ ውስጥ አስገባቻቸውና ወደ ባሕር ወረወረቻቸው።
ሙሳና ወንድሙ ሃሩንም ወደ ፊርዓውን – ትዕቢተኛው ንጉሥ – ሄደው የዓለማቱ ጌታ አላህን እንዲገዛ ጥሪ (ዳዕዋ) አደረጉለት።
{ፈርዖን አለ «(ላከኝ የምትለው) የዓለማትም ጌታ ምንድነው»}
{(ሙሳ) «የሰማያትና የምድር በመካከላቸውም ያለው ሁሉ ጌታ ነው። የምታረጋግጡ ብትኾኑ (ነገሩ ይህ ነው)፤» አለው።}
{(ፈርዖንም) በዙሪያው ላሉት ሰዎች «አትሰሙምን» አለ።}
{(ሙሳ) «ጌታችሁና የመጀመሪያዎቹ አባቶቻችሁም ጌታ ነው» አለው።}
{(ፈርዖን) «ያ ወደእናንተ የተላከው መልክተኛችሁ በእርግጥ ዕብድ ነው» አለ።}
{(ሙሳ) «የምሥራቅና የምዕራብ በመካከላቸውም ያለው ነገር ሁሉ ጌታ ነው። ታውቁ እንደኾናችሁ (እመኑበት)» አለው።}
{(ፈርዖን) «ከእኔ ሌላ አምላክን ብትይዝ በውነቱ ከእስረኞቹ አደርግሃለሁ» አለ።}
{(ሙሳ) «በግልጽ አስረጅ ብመጣህም እንኳ» አለው።}
{«እንግዲያውስ ከእውነተኞች እንደኾንክ (አስረጁን) አምጣው» አለ።}
{በትሩንም ጣለ። እርስዋም ወዲያውኑ ግልጽ እባብ ኾነች።}
{እጁንም አወጣ። እርሷም ወዲያውኑ ለተመልካቾች ነጭ ኾነች።}
{(ፈርዖን) በዙሪያው ላሉት መማክርት «ይህ በእርግጥ ዐዋቂ ድግምተኛ ነው» አለ።}
{«ከምድራችሁ በድግምቱ ሊያወጣችሁ ይፈልጋልና ምንን ታዛላችሁ» (አላቸው)።}
{አሉት «እርሱን ወንድሙንም አቆይና በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን ላክ።}
{«በጣም ዐዋቂ ድግምተኞችን ሁሉ ያመጡልሃልና።»}
{ድግምተኞቹም በታወቀ ቀን ቀጠሮ ተሰበሰቡ።}
{ለሰዎቹም «እናንተ ተሰብስባችኋልን» ተባለ።}
{«ድግምተኞቹን እነሱ አሸናፊዎች ቢኾኑ እንከተል ዘንድ» (ተባለ)።}
{«ድግምተኞቹም በመጡ ጊዜ ለፈርዖን እኛ አሸናፊዎች ብንሆን ለእኛ በእርግጥ ዋጋ አለን» አሉት።}
{«አዎን፤ እናንተም ያን ጊዜ ከባለሟሎቹ ትኾናላችሁ» አላቸው።}
{ሙሳ «ለእነርሱ እናንተ የምትጥሉትን ጣሉ» አላቸው።}
{ገመዶቻቸውንና በትሮቻቸውንም ጣሉ። «በፈርዖንም ክብር ይኹንብን። እኛ በእርግጥ አሸናፊዎቹ እኛ ነን» አሉ።}
{ሙሳም በትሩን ጣለ። ወዲያውም እርሷ የሚያስመስሉትን ሁሉ ትውጣለች።}
{ድግምተኞቹም ሰጋጆች ኾነው ወደቁ።}
{አሉ፡- «በዓለማት ጌታ አመንን።»}
{«በሙሳና በሃሩን ጌታ።»}
{(ፈርዖንም) «ለእናንተ ሳልፈቅድላችሁ በፊት ለእርሱ አመናችሁን እርሱ ያ ድግምትን ያስተማራችሁ ታላቃችሁ ነው። ወደፊትም (የሚያገኛችሁን) በእርግጥ ታውቃላችሁ። እጆቻችሁንና እግሮቻችሁን (ቀኝና ግራን) በማናጋት እቆረርጣለሁ። ሁላችሁንም እሰቅላችኋለሁም» አለ።}
{(እነርሱም) አሉ «ጉዳት የለብንም። እኛ ወደ ጌታችን ተመላሾች ነን።}
{«እኛ የምእምናን መጀመሪያ በመኾናችን ጌታችን ኀጢአቶቻችንን ለእኛ ሊምር እንከጅላለን።»}
{ወደ ሙሳም «ባሮቼን ይዘህ ሌሊት ኺድ። እናንተ የሚከተሉዋችሁ ናችሁና» ስንል ላክን።}
{ፈርዖንም በየከተሞቹ ሰብሳቢዎችን (እንዲህ ሲል) ላከ።}
{«እነዚህ ጥቂቶች ጭፈሮች ናቸው።}
{«እነርሱም ለእኛ አስቆጪዎች ናቸው።}
{«እኛም ብዙዎች ጥንቁቆች ነን፤» (አለ)።}
{አወጣናቸውም። ከአትክልቶችና ከምንጮች።}
{ከድልቦችም ከመልካም መቀመጫዎችም።}
{እንደዚሁ ለእስራኤል ልጆች አወረስናትም።}
{ፀሐይዋ ስትወጣም ተከተሉዋቸው።}
{ሁለቱ ጭፍሮችም በተያዩ ጊዜ የሙሳ ጓዶች «እኛ(የፈርዖን ሰዎች) የሚደርሱብን ነን» አሉ።}
{(ሙሳ) «ተዉዉ! ጌታዬ ከእኔ ጋር ነው። በእርግጥ ይመራኛል» አለ።}
{ወደ ሙሳም «ባሕሩን በበትርህ ምታው» ስንል ላክንበት። (መታውና) ተከፈለም። ክፍሉም ሁሉ እንደ ታላቅ ጋራ ኾነ።}
{እዚያም ዘንድ ሌሎችን አቀረብን።}
{ሙሳንም ከእርሱ ገር ያሉትንም ሰዎች ሁሉንም አዳን።}
{ከዚያም ሌሎቹን አሰጠምን።}
{በዚህ ውስጥ ታላቅ ታምር አለበት። አብዛኞቻቸውም አማኞች አልነበሩም።}
{ጌታህም እርሱ በእርግጥ አሸናፊ አዛኝ ነው።}
[አሽ_ሹዓራእ፡ 23_67]
ፊርዓውንም መስመጡን ባወቀ ጊዜ፡- የእስራኤል ልጆች ካመኑበት አምላክ በቀር ሌላ አምላክ እንደሌለ አምኛለሁ። አለ። የላቀው አላህ እንዲህ ነግሮናል፦
{ከአሁን በፊት በእርግጥ ያመጽክ ከአጥፊዎችም የነበርክ ስትሆን አሁን (አመንኩ ትላለህ)}
{ዛሬማ ከኋላህ ላሉት ተዓምር ትሆን ዘንድ በድን ሆነህ (ከባሕሩ) እናወጣሃለን (ተባለ)። ከሰዎችም ብዙዎቹ ከተዓምራታችን በእርግጥ ዘንጊዎች ናቸው።} (ዩኑስ፡ 91-92)
አላህም ያች ምሥራቋንም ምዕራቧንም በረካ ያደረገባትን አገር ለነዚያ ለተጨቆኑት (ለሙሴ ሕዝቦች) አወረሳት። ለፊርዓውንና ለህዝቦቹም ይሰሩት የነበረውን (ህንፃ) ዳስ ያደርጉት የነበረውንም አጠፋ።
ከዚህም በኋላ አላህ ለሙሳ በውስጧ ሰዎችን አላህ ወደሚወደውና ወደሚቀበለው የሚያመላክት መመሪያና ብርሃን ያለባት፤ የእስራኤል ዝርዮች (የሙሳ ህዝቦች) ሊከተሉት ግዴታ የሆነባቸው የሐላልና የሐራም ማብራርያ አድርጎ የተውራትን መጽሐፍ አወረደ።
ከዚያም ሙሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ሞቱና አላህም ከእርሳቸው በኋላ ለህዝባቸው – ለእስራኤል ልጆች – አንዱ በጠፋ ቁጥር በሌላኛው ነብይ እየተተካ ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመሩ ብዙ ነብያቶችን ላከ።
አላህ እንደ ዳውድ፣ ሱለይማን፣ አዩብና ዘከሪያ ያሉትን ጥቂቶቹን የተረከልን ሲሆን ከነብያቶች ያልተረከልን ብዙዎችም አሉ። ከዚያም እነዚህን ተከታታይ ነብያት ከውልደቱ ጀምሮ ወደ ሰማይ እስካረገበት ጊዜ ድረስ ሕይወታቸው በብዙ ተአምራት በተሞላው በዒሳ ብን መርየም (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) አጠናቀቀ።
አላህ ለሙሳ በትውልዶች የገለጠው ተውራት የሙሳ (የአላህ ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ተከታዮች ነን በሚሉ ሙሳም ከእነሱ የጠሩ በሆኑት አይሁዶች እጅ መዛባትና መበረዝ ተጋረጠበት። በእጃቸው ያለው ተውራት ደግሞ ከአላህ ዘንድ የተወረደው ተውራት ተደርጎ አይቆጠርም፤ በውስጡ ለአላህ የማይገቡ ነገራቶችን አስገብተዋል፤ አላህንም በእንከን፣ ባለማወቅና በድክመት ባህሪያት ገልፀውታልና – አላህ እነርሱ ከሚሉት የላቀ ጥራት ይገባውና – ልዕለ ኋያሉ አላህ እነርሱን እንዲህ ሲል ነው የገለፃቸው፦
{ለነዚያም መጽሐፉን በእጆቻቸው ለሚጽፉና ከዚያም በርሱ ጥቂትን ዋጋ ሊገዙበት «ይህ ከአላህ ዘንድ ነው» ለሚሉ ወዮላቸው። ለነርሱም ከዚያ እጆቻቸው ከጻፉት ወዮላቸው። ለነሱም ከዚያ ከሚያፈሩት (ኃጢኣት) ወዮላቸው።}
[አል-በቀራህ፡ 79]